አርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 21ኛውን ዓለም አቀፍ ዘላቂ የውኃ ሀብት ልማት ሲምፖዚየም ከሰኔ 02-03/2015 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደተናገሩት አርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት በውኃው መስክ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ የቆየ ሲሆን በተለይ በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በውኃ ኃይል ማመንጫ፣ መስኖና ሌሎች  የተለያዩ የውኃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች ላይ የበኩሉን አስተዋጾ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ሲምፖዚየሙ የውኃ ሀብታችንን ለሀገር እድገትና ብልጽግና ለማዋል የዘርፉ ችግሮች፣ መፍትሔዎች፣ አዳዲስ አሠራሮች፣ ዕውቀቶች እና የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ላይ በመወያየት የዕውቀት ሽግግር የምናደርግበት ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ባቀረቡት ቁልፍ መልእክት ሀገራችን ካሏት 12 የውኃ ተፋሰሶች ከአዋሽና ከስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች በስተቀር ከ75 በመቶ በላይ የውኃ ሀብታችን ድንበር ተሻግሮ እንደሚሄድ ተናግረው በሀገራችን ያለው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ከ62 የማያልፍ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ድንበር ተሸጋሪ የውኃ ሀብቶቿን በአግባቡ ለኃይል ማመንጫ፣ ለመስኖ፣ ለኢንደስትሪ፣ ለዓሣ ሀብት፣ ለቱሪዝምና ለሌሎች አግልግሎቶች በዘላቂነት ለማልማት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው የቁልፍ ንግግር አቅራቢ ከካናዳ ማክማስተር ዩኒቨርሲቲ/McMaster University/ የመጡት ፕ/ር ፓውሊን ኮውሊባሊ/Prof. Paulin Coulibaly/ ‹‹Current Challenges in Water Resources, Research, Development and Management›› በሚል ርእስ ባቀረቡት መልእክት በውኃ ሀብት ምርምር፣ ልማትና አስተዳደር ላይ ያሉ ወቅታዊ ተግዳሮቶችና የተመራማሪዎች ሚና እንዲሁም  የውኃ ሀብትን መቆጣጠርና በትክክል መገመት የሚሉ ቁልፍ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የውኃ ምርምርና ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሮ ሜሮን ተፈራ ‹‹Case for Collaboration Between Data Providers and Users to Enhance Streamflow Data Availability in Ethiopia›› በሚል ርእስ ያቀረቡት ጥናት የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊነት ካላቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመተባበር የውኃ ሀብት መረጃ መሰብሰብ፣ መተንተንና ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ ተሞክሮዎችን ማሳያ አድርጎ ያቀረበ ነው፡፡

ሌላኛዋ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውኃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ ተመራማሪ መምህርት ምንታምር ፈረደ ‹‹Implication of Uncontrolled Water Withdrawal and Climate Change on the Water Supply and Demand Gap in the Lake Tana Sub-basin›› በሚል ርእስ ያቀረቡት ጽሑፍ በአንድ መንደር ያሉ አርሶ አደሮች በአየር ንብረት ለውጥና ውኃን ቆጥቦ ባለመጠቀም ምክንያት ችግር ሳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል በአካባቢው ያለውን የውኃ መጠን በማጥናት ለመጠጥና ለመስኖ የሚውለውን ለይቶ በአግባቡ መጠቀምና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም በውኃ እጥረት ምክንያት የሚከሰትን ግጭት ማስወገድ እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ከተለያዩ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን 21 የምርምር ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት