የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጃፓይጎ ‹‹Jhpiego›› ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር የሴት መምህራን ፎረም/Women Academic Forum/ ለመመሥረት ሰኔ 02/2015 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ፎረሙ ሴቶች ያላቸውን የመምራት ችሎታ በማሳደግ አቅማቸውን እንደሚገነባ ጠቅሰው ከቀደሙት የተለያዩ ልምዶችን በመውሰድ ፎረሙ እንዲጠናከር ሴት ተማሪዎችንና የአስተዳደር ሠራተኞችን አቅፎ ሰፋ ያለ ሥራ እንዲሠራ ይደገፋል ብለዋል፡፡

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወሪ/ት ሠናይት ሳህሌ ሴቶች ችሎታና አቅማቸውን ተጠቅመው ማደግና መለወጥ ብሎም ለቤተሰብ፣ ለሀገርና ለዓለም የበኩላቸውን ማበርከት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ሴቶች ወደ ፊት እንዲመጡ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሠራ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ሴቶች በአመራርነት የማስፈጸም አቅምን በማጎልበት የራሳቸውን ሚና ለመወጣት በትጋት መሥራት፣ የምርምር ክሂሎታቸውን ማዳበርና መሠረታዊ ዕውቀት መጨበጥ እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ዳይሬክተሯ በውይይቱ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከበላይ አካላት ጋር በመሆን እንሠራለን ብለዋል፡፡

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ላቦራቶሪ ሳይንስ ት/ክፍል መምህርትና የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ወ/ሪት ገሊላ ቢረሳው የሴት መምህራን ፎረም መመሥረትና  ጠንካራ ሆኖ መውጣት የፎረሙ ዓላማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አስተባባሪዋ እንደ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመድፈን በመግባባት በመሥራት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶችና ከዩኒቨርሲቲውም ውጪ በማጋራት መልካም ተጽዕኖ ለማሳደር እንሠራለን ብለዋል፡፡ ፎረሙ የጤና ባለሙያዎች ተገቢውን ክሂሎትና አመለካከት አግኝተው እንዲወጡ የሚያስችል፣ ለሴት መምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን የመስጠት፣ መምህራን እርስ በእርስ ተቀራርበው የሚሠሩበትን መድረክ የመፍጠርና የተለያዩ ድጋፎችን የማድረግ ተግባራትን ከጃፓይጎ ጋር በትብብር ያከናውናል፡፡

በመድረኩ ፎረሙ ምን እንደሚሠራ፣ ዓላማው፣ አስፈላጊነቱና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ መ/ርት ቤተልሔም ሲራክ የፎረሙ ሰብሳቢና መ/ርት ሕይወት ታደሰ ም/ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት