አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቆላ ሻራ ቀበሌ እያካሄደ የሚገኘውን የቆላ ሻራ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክት የማጠናቀቂያ ሥራዎች አፈጻጸም የመስክ ምልከታ ሰኔ 9/2015 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የውሃ ፕሮጀክቱ ከፊል ሥራው ተሠርቶ ወደ አገልግሎት ሳይገባ የቆየ መሆኑን አስታውሰው የፕሮጀክቱን ቀሪ ሥራዎች ለማጠናቀቅ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቅድሚያ ተሰጥቶት በትኩረት እንዲሠራ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬትና የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንሱን ወደ መሬት አውርደው ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ በመሥራታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በቅርቡ ተጠናቆ ለማኅበረሰቡ የሚተላለፍ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ የተሠራው ልማት ረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ በጥንቃቄና በኃላፊነት መጠቀምና በአግባቡ መንካባከብ ይገባል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የቆላ ሻራ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ሥራ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ቢጀመርም ከበጀት አቅም ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቱ በጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ ከማኅበረሰቡ ጥያቄ መቅረቡን ያስታወሱት ዶ/ር ተክሉ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ጥያቄውን ተቀብሎ ፕሮጀክቱ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራና ተጠናቆ በአገልግሎት ላይ እንዲውል እንዲደረግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የተሠራውን ሥራ ያለበትን ደረጃ ለመገምገም የመስክ ምልከታው ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡  

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የቀድሞ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርና የቆላ ሻራ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክት የቴክኒክ ሥራ ቡድን መሪ ዶ/ር አብደላ ከማል በቀረበው ጥያቄ መሠረት ማኔጅመንቱ የሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመለየት የ15 ቀናት ጥናት ተደርጓል ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አብደላ ፕሮጀክቱ ወጪ ቆጣቢና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ እንዲሁም ለቀጣይ 20  እና 30 ዓመታት የሚኖረውን የከተማውንና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ተገንብቶ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ሳይንቲፊክ ዳሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ማኅበረሰብን ማገልገል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ የትኩረት መስክ እንደመሆኑ እንደ ኢንስቲትዩት በዲዛይን ዝግጅት፣ በኮንስትረክሽንና በሌሎችም ዘርፎች ሙያዊ አገልግሎት እየሰጠን ነው ብለዋል፡፡ የውሃ አቅርቦት ሥራ በአንዴ ተሠርቶ የሚጠናቀቅ አይደለም ያሉት ዶ/ር ቦጋለ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር እየተጣጣመ እንዲሄድ በየጊዜው ጥናት እየተደረገ ሌሎች የውሃ ጉድጓዶች የመቆፈር፣ የውሃ መስመር ዝርጋታና ተጨማሪ ገንዳዎችን መገንባት ሥራዎች የሚጠበቁ ስለሆነ ኢንስቲትዩቱ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ማናዬ ዳርጫ የቆላ ሻራ ቀበሌ ነዋሪና የመጠጥ ውሃ ግንባታ ኮሚቴ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤትን በማመስገን ቆላ ሻራ ቀበሌ ከፍተኛ የውሃ ችግር የነበረ ሲሆን ማኅበረሰቡም አቅም ያለው እስከ አ/ምንጭ ከተማ በመሄድ ቧንቧ የመጠቀም አቅም የሌላውም በአካባቢው የሚያገኘውን ንጽሕናው ያልተረጋገጠ ውሃ ከወንዝ እየቀዳ ለመጠቀም የተገደደ ነበር ብለዋል፡፡ ይህም የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ከባድ ያደረገ የነበረ መሆኑን ጠቅሰው የመጠጥ ውሃው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ መሆን አቶ ማናዬ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መ/ርት ፌቨን ክንፈ ከማጠራቀሚያ ገንዳ በኋላ ውሃውን የማሠራጨት ሥራን ዩኒቨርሲቲው ተቀብሎ ማከናወኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ በዚህም በ3.2 ሚሊየን ብር የአስፈላጊ ዕቃዎች ግዥ ተፈጽሞ የ10 ኪ.ሜ የውሃ ስርጭት መስመር ዝርጋታ ሥራ፣ ለጉልበትና ለቧንቧ ሠራተኞች እንዲሁም ግምበኞች ክፍያ የመፈጸምና የዲዛይን ሥራዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 3.69 ሚሊየን ብር ከዩኒቨርሲቲው ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡  የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮውን፣ የ1.75 ከ.ሜ ወደ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውሃ ማስገቢያ ዋና መስመር ዝርጋታና 200 ሺህ ሊትር የሚይዝ የውሃ ገንዳ ግንባታ የአርባ ምንጭ ዙ/ወ/ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ቀደም ብሎ በያዘው ፕሮጀክት የሠራው መሆኑን መ/ርት ፌዘን ጠቅሰዋል፡፡ ዳይሬክተሯ አክለው እንደተናገሩት የአካባቢው ማኅበረሰብም አጋዥ ኮሚቴ በማዋቀር የስርጭት መስመር ቁፋሮ ሥራ፣ የሲሚንቶ፣ አሸዋና ሌሎች ግብዓቶች ከቦታ ቦታ እንደ አስፈላጊነቱ በጉልበቱ የማንቀሳቀስ እንዲሁም በነፍስ ወከፍ 1,000.00 ብር በማዋጣት ትራንስፎርሜር መግዛቱን በመግለጽ ኮሚቴውና ማኅበረሰቡ ለሥራው መሳካት ስላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡  

በመስክ ምልከታው የዩኒቨርሲቲውን ፕሬደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛን ጨምሮ ም/ፕሬዝደንቶች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮችና የሥራ ክፍል ዳይሬክተሮች፣ ባለሙያዎችና የቀበሌው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት