የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ጋር በመተባበር ለኮሌጁ መምራን “Grant Proposal Writing and Manuscript Preparation Skills” በሚል ርዕስ ከሰኔ 8-9/2015 ዓ/ም የክሂሎት ማሻሻያ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡  በዕለቱም ከአሶሴሽኑ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የሙያ ማኅበራት ከዘርፉ መጠናከር፣ ከትምህርት ጥራት እና ከሀገር ተጠቃሚነት አንጻር  ያላቸው ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰው የሥልጠናው ትኩረትም ለተቋሙ ወቅታዊና አግባብነት ያለው በመሆኑ ጥሩ የልምድ መጋራት ሂደት የሚከወንበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የጋራ  ስምምነቱን መሠረት በማድረግ ዘርፉ እንዲጠናከር አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕ/ር መንግሥቱ ለማ ድጋፍ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶች አዘገጃጀትና አስተዳደር እንዲሁም የምርምር ጽሑፍ ኅትመት አዘገጃጀት ላይ በሰጡት ሥልጠና ወቅቱን መሠረት በማድረግ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን ክሂሎት በማሳደግ የሰው ሀብት፣ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ላይ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አስተዳደርን ተግባራዊ ሲያደርጉ የሚያጋጥመውን የበጀት ዕጥረት ለመሸፈን ያስችል ዘንድ መምህራን ግራንት ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ፕ/ር መንግሥቱ አክለውም መምህራን በሥልጠናው በመታገዝ ከመማር ማስተማር በተጨማሪ ድጋፍ ሰጪ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን /Grand Projects/ በማምጣትና ምርምሮችን በመሥራት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ታዋቂ ጆርናሎች ላይ በማሳተም ራሳቸውን፣ ተቋሙን እና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡ የኢትየጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽንም ተቋማትን በመደገፍ እና በጋራ በመተባበር የኢኮኖሚክስ ትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ አስተዋጽዖ ማድረግ እና ምርምሮች እንዲሠሩ ማድረግ ዋና ተግባሩ እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በሚኖሩት የሥራ ጊዜያትም በጋራ ፕሮጀክቶችን በመጻጻፍና በመቅረጽ፣ ኮንፍረንሶችን በማዘጋጀትና መሰል ተግባራትን በማከወን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ በበኩላቸው ተቋሙ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ከመሆኑም ባሻገር  ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር እያመራ በመሆኑ በኮሌጁ ያሉ ወጣትና አዳዲስ መምህራን በተለያየ ዘርፍ ልምዶችን እንዲያገኙና የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ለማስቻል ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን በርካታ ለሀገር ልማትና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጠቃሚ ተግባራትን የሚያከናውን በመሆኑ በዘርፉ ያለውን ልምድና የአሠራር ሂደት ወደ ተቋሙ ለማምጣት እንደ ኮሌጅ እየሠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ የሥራ ክፍሎች አባል በመሆንም በቀጣይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እና በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን በጋራ ለመሥራት የውል ስምምነቱ መፈጸሙን ዲኑ አመላክተዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ር ስለሺ አበበ በበኩላቸው መምህራኑ የውስጥ ምርምሮችን እየሠሩ ቢሆንም በአብዛኛው ግራንትና የትብብር ፕሮጀክቶችን ፈልጎ የመሥራት ልምዱ አናሳ በመሆኑ  የግራንት ንድፈ ሃሳብ አጻጻፍ እና የኅትመት ሪፖርት አዘገጃጀት ላይ  በመሳተፍ  ያለባቸውን  የክሂሎት  ክፍተት መሙላት እንዲችሉና የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው በዘርፉ በቂ ዕውቀትና ልምድ ባላቸው አሠልጣኝ ሥልጠናው እንዲሠጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊ የነበሩት ወ/ሮ አምሳል ተክሌና አቶ ዋጋው ደምለው በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው በቀጣይ ለሚሠሩት የምርምር ሥራዎች ግብዓት የሚሆናቸውን መሠረታዊ የሆነ ዕውቀት እንዳገኙ ገልጸው የበጀት ዕጥረትና ራስ ገዝ አስተዳደር እየመጣ ባለበት ጊዜ ግራንት ፕሮጀክቶችን ማምጣትና በጀት አፈላልጎ በማግኘት ዘርፈ ብዙ ምርምሮችን መሥራት እንደ ሀገር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

በሥልጠናው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲንና መምህራን እንዲሁም የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት