አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአባልነት የተካተተበት እንሰትን ብሔራዊ ስትራቴጂክ ሰብል ለማድረግ የተቋቋመው የእንሰት ፍላግሺፕ ፕሮግራም ከሚቴ አባላት ዩኒቨርሲቲው በመስኩ እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን በምርምር ቤተ-ሙከራዎችና ሠርቶ ማሳያዎች ላይ በመገኘት ከሰኔ 11-12/2015 ዓ/ም ምልከታና የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ዩኒቨርሲቲው በእንሰት ዙሪያ ለሚደረጉ ምርምሮችና የቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረው እንሰት በዚህ ልክ ሀገራዊ ትኩረት ማግኘቱ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው በሀገራዊ የእንሰት ፍላግሺፕ ፕሮግራም አዘጋጅ ኮሚቴ አባል መሆኑ በእጅጉ የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በግብርና ኮሌጅ በኩል የእንሰት ጉዳይ በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ እንደሚሠራም ዶ/ር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ አክለው እንደተናገሩት  ከኮሚቴው አባላት የተሰጡ አስተያየቶች እንደ ተቋም በርካታ ግብዓቶች የተገኙበት ሲሆን በቀጣይ በጋራ ለመሥራት የተጀመሩ ግንኙነቶችን ተቋማዊ ማድረግ ይገባል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብደላ ነጋሽ በግብርና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከተለያዩ የምርምርና ከመስኩ መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ተመራማሪዎችንና የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ 12 አባላት ያሉት እንሰትን ሀገር አቀፍ ሰብል ለማድረግ የሚያግዝ የእንሰት ፍላግሺፕ ፕሮግራም ሠነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገለጸዋል፡፡ ሠነዱ በዋናነት የእንሰት ምርትና ምርታማነትን ማሳዳግ፣ የድኅረ-ምርት አሰባሰብ ሂደቶችን በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የግብይት ሂደትና ዕሴት መጨመርንና ከፕሮጀክት አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው አውስተዋል፡፡

የመስክ ምልከታው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመስኩ የሚያከናውናቸውን የምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን ምልከታ በማድረግ እየተዘጋጀ ለሚገኘው ሀገር አቀፍ ፕሮግራም ተጨማሪ ግብዓቶችን ለማግኘት የተሠናዳ መሆኑን የገለጹት አቶ አብደላ ዩኒቨርሲቲው ከበሽታ የጸዱ የእንሰት ችግኞችን ለማኅበረሰቡ ለማዳረስ እያደረገ ያለው ጥረትና ጥናት፣ የተለያዩ የእንሰት ዝርያዎችን በቆላማ አካባቢዎች ለማላመድ እየተሠራ ያለው ሥራ እንዲሁም የድኅረ-ምርት አሰባሰብና ማብላላት ሂደትን ለማዘመን የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች በእጅጉ የሚደንቁና እንደ ሀገር ሊሰፉ የሚገባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የነበረን የሁለት ቀናት ቆይታ በቀጣይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በእንሰትና በሌሎች የሆርቲካለቸር ልማት ዘርፎች የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምርና ልማት ሥራዎችን በትብብር ለመሥራት ያነሳሳቸው መሆኑንም አቶ አብደላ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና የምርምርና ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ዩኒቨርሲቲው እንሰት ላይ ከሚሠራቸው ሰፋፊ ሥራዎች አንፃር ከዩኒቨርሲቲዎች ብቸኛው የብሔራዊ የእንሰት ፍላግሺፕ ፕሮግራም አዘጋጅ ኮሚቴ አባል መሆኑ በመስኩ ከሠራቸው ሥራዎች አንፃር የሚገባውና እንደ ተቋም ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንሰት ከምግብነት ባሻገር ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር እንደ ዩኒቨርሲቲ የዚህ ሀገር አቀፍ ኮሚቴ አባል መሆናችን ሰብሉ እንዲሁም የሠራናቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመላው ሀገሪቱ እንዲስፋፉ ያለንን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሳካት በር የከፈተ እንደሆነም ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ እንደ ምርምር ተቋም ከኮሚቴው አባላት የተሰጡን አስተያየቶች አዳዲስ ምርምሮችን ለመሥራት አቅጣጫዎችን ያመላከቱ፣ በሂደት ያሉ የምርምር ሥራዎች ላይ የቅርጽ ለውጥ ለማድረግ የሚረዱ እንዲሁም ትኩረት ማድረግ ያሉብንን የምርምር መስኮችን እንድንለይ የሚያስችሉና ሌሎች በርካታ ግብዓቶች የተገኙበት መሆኑን ዶ/ር ተስፋዬ ጠቅሰዋል፡፡ የምሁራኑና የሥራ ኃላፊዎቹ ጉብኝት የእንሰት ምርምርን በተለየ ሁኔታ መደገፍ እንዳለብን ያመላከተ ሲሆን በቀጣይ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለሚኖሩን የትብብር ሥራዎች በር የከፈተና የትብብር መነሻ ሃሳቦች የተነሱበት መሆኑንም ዶ/ር ተስፋዬ አመላክተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪና የኮሚቴው አባል ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንሰት የደቡብ፣ የደቡብ ምዕራብ፣ የኦሮሚያና የሲዳማ ብቻ ክልሎች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ምግብ ሊሆን ስለሚገባው እንዲሁም በስንዴና መሰል ሰብሎች ላይ የተፈጠረው ሀገራዊ መነሳሳት እንሰት ላይ ለመድገም በማለም በሀገር አቀፍ ደረጃ የእንሰት ፍላግሺፕ ፕሮግራም በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ እየተዘጋጀ በሚገኘው ሠነድ ላይ የዩኒቨርሲቲው ተሞክሮ ጎልቶ የወጣ በመሆኑ የኮሚቴው አባላት ሥራውን በአካል ተገኝቶ ለማረጋገጥና ተጨማሪ ግብዓት ለማግኘት ተልዕኮ ይዘው በዩኒቨርሲቲው መገኘታቸውን ዶ/ር አዲሱ ጠቁመዋል፡፡ በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የኮሚቴው አባላት ነባር ተማራማሪዎች፣ የፕሮግራም መሪዎች፣ አማካሪዎችና የምርምር ተቋማት ዳይሬክተሮችና የሥራ ኃላፊዎች በመሆናቸው በምልከታቸው ወቅት ማረጋገጥ እንደተቻለው ከግብርና ሚኒስቴር ጨምሮ ከሌሎች የኮሚቴው አባላት ተወክለው ከመጡባቸው ተቋማት ጋር ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ የትብብር ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እንዲሠራ በር የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምልከታው ወቅት የተሰጡ አስተያየቶችና አድናቆቶች ለቀጣይ ሥራዎች የሚያነሳሱና ተጨማሪ የምርምር አቅጣጫዎችን የጠቆሙ መሆኑንም ዶ/ር አዲሱ ጠቅሰዋል፡፡

የሀዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዘሪሁን የማታው በሰጡት አስተያየት የእንሰት አጠውልግ በሽታና ባህላዊው የሰብሉ የመፋቅና የማብላላት ሂደቶች ዋነኛ ማነቆዎች ሲሆኑ ተክሉ የሚሰጠውን ጥቅም ያክል ተገቢውን ድጋፍ እያገኘ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ እነዚህንና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው በመስኩ ያከናወናቸው የምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች እንደ ሀገር እየተዘጋጀ ለሚገኘው ፕሮግራም ትልቅ ግብዓትና መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ መሆኑን በምልከታቸው እንዳረጋገጡ ዶ/ር ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡  

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር መኩሪያ ታደሰ በበኩላቸው እንሰት እንደ ሌሎች ሰብሎች ያደገ አለመሆኑና እንደ ሀገር መጠቀም ያለብንን ያህል ጥቅም ያልሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንሰትን በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ሀገራዊ ስትራቴጂክ ሰብል ለማድረግ በግብርና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሀገር አቀፍ የእንሰት ፍላግሺፕ ፕሮግራም እየተዘጋጀ መሆኑ ከዚህ አንፃር በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመስኩ እያከናወናቸው ባሉት ተግባራት ዙሪያ ቀደም ብሎም በተለያዩ መንገዶች መረጃ የነበራቸው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መኩሪያ በአካል መጥተው ያዩት ነገር ግን ከጠበቁት በላይ እንደሆነባቸውና በተለይ ከእንሰት የተሠሩት ዕሴት የተጨመረባቸው ምግቦች እንዲሁም የመፋቅና የማብላላት ሂደቱን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ፣ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት የሚያግዙ መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎችና የፈጠራ ሥራዎችን ሀገራዊ ለማድረግ በትብብር መሥራት እንደሚገባ እንዲሁም ከበሽታ ነፃ የሆኑ ዝርያዎችን በቲሹ ካልቸር በማባዛት ማስፋት ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ ሊሠራ እንደሚገባም ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት