በዓለም ለ19ኛ በሀገራችን ለ11ኛ ጊዜ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድን የመከላከልና መቆጣጠር ቀን/Antimicrobial Resistance Day/ "የአመራር ሚና የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድን ለመከላከልና መቆጣጠር" በሚል መሪ ቃል ከኢትዮጵያ ፋርማሲዎች ማኅበር፣ ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፋርማሲ ት/ክፍልና ከኢትዮጵያ ፋርማሲ ተማሪዎች ማኅበር ጋር በመተባበር ሰኔ 12/2015 ዓ.ም ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለፁት በፋርማሲ ት/ክፍል ይህ ፕሮግራም መዘጋጀቱ እንደ ኮሌጅ የሚያኮራ መሆኑን ገልጸው የጀርሞች የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶችን የመላማድ ሁኔታ/Antimicrobial Resistance/ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የሚባል የስጋት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም የሁሉም ዓይነት ጀርሞች ሕክምና ባለሙያዎች ተሰብስበው በምርምር ውጤቶች ላይ በመነጋገር በዓሉን ማክበር በራሱ የመፍትሄ አካል ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸውም ዶ/ር ታምሩ ተናግረዋል ፡፡

ከኢትዮጵያ ፋርማሲዎች ማኅበር ተወክለው የመጡት በክሊኒካል ፋርማሲ ረ/ፕ ግሩም ተስፋዬ የዘንድሮ መሪ ቃል  የተመረጠበት ምክንያት መሪዎቻችን የጀርሞች የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድን የመከላከልና መቆጣጠር ሚናን በራሳቸው በመውሰድ በተፈለገው መጠን ችግሩን መቆጣጠርም መከላከልም እንደሚቻል ገልፀው እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት በ2019 እ.ኤ.አ ብቻ አምስት ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ጀርሞች የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶችን በመላማድ ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡ አሁንም በጊዜ ካልሠራንበትና ካልተከላከልን እስከ 2050 እ.ኤ.አ እስከ 10 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በተመሳሳይ ችግር ምክንያት ሊሞቱ እንደሚችሉ ሪፖርቱ እንደሚያሳይ ጠቅሰው መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ የንጽሕና አጠባበቅ መንገዶችን ማሻሻል፣ ምርምርና ጥናቶችን መሥራት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መሥራት እና ስለጀርሞች የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶችን መላመድ ስለሚያመጣው አደጋ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት መሪዎች ኃላፊነት ወስደው እንዲያስተግብሩ የሚጠበቁ አምስት የመፍትሄ ተግባራት መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

ረ/ፕ ግሩም አክለውም የግብርና፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የእንስሳት ጤና ተቋማትና የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ዘርፎቹን ስለሚመለከት በትብብር መሥራት ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚረዳ ተናግረው የመድኃኒትን አጠቃቀም ከሐኪም፣ ከነርስና ከፋርማሲስቱ መቀበል እንደሚጠበቅ እንዲሁም ማኅበረሰቡ የታዘዘውን መድኃኒት በታዘዘው ሰዓትና ቀን መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡
በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ የፋርማሲ ት/ክፍል ኃላፊ መ/ር ቴዎድሮስ አግደው እንደ ት/ክፍል ፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶችን በተመለከተና የጤና ትምህርቶችን በየሆስፒታሉ የመስጠት የመሳሳሉ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ መቆየታቸውን ገልፀው 11ኛው የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድን የመከላከልና መቆጣጠር  ቀን/ Antimicrobial Resistance Day/ ማክበር የማኅበረሰቡ መድኃኒቶችን ያለአግባብ መጠቀም መድኃኒቶቹን ሰውነት እንዲለማመድ የሚያደርግ ሲሆን ይህም ከጤናና ኢኮኖሚ አንፃር ያለው ጉዳት ከፍተኛ ስለሆነ ግንዘቤ ለማስጨበጥ ሳምንቱንም የ/Antimicrobial Resistance Week/ ብለው ማክበር መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ የፋርማሲ ት/ክፍል መምህር አቶ ደባልቄ ዳላ “HAART and HIV-Drug Resistance and Global, Regional Impact” በሚል ርዕስ ባቀረቡት የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ለኤች አይ ቪ ቫይረስ የምንጠቀማቸውን መድኃኒቶች የተላመደ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ቁጥር ትልቅ መሆኑንና ከፍ ያለ መዘናጋትም እንደሚስተዋል ገልጸዋል፡፡ መ/ር ደባልቄ አክለውም HIV የማይድን በሽታ እንደመሆኑ ሰዎች መድኃኒት ከጀመሩ በኋላ በሽታው የተሻላቸው ቢመስል እንኳን መድኃኒታቸውን በአግባቡ መውሰድና አለማቋረጥ መድኃኒት የተላመደ HIVን በመቀነስ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ በፕሮግራም መጨረሻም ተማሪዎች የኅብረት ጉዞ በማድረግ በከተማ ውስጥና በሆስፒታሎች በመገኘት የግንዛቤ መፍጠር ዘመቻ አካሂደዋል፡፡ ማኅበሩን የሚከታተሉ፣ የሚሠሩና የሚመለከታቸው አካላትን የሚያሳትፉ የፋርማሲ ተማሪዎች ማኅበር ተወካዮችም ተመርጠዋል፡፡

በፕሮግራሙ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩንና ሌሎች የኮሌጁ አመራር አካላትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ፋርማሲዎች ማኅበር የመጡ እንግዶችና የዩኒቨርሲቲው የፋርማሲ ት/ክፍል መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት