በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል ‹‹English Language Teaching /ELT/›› የትምህርት ፕሮግራም ላለፉት 5 ዓመታት የ3ኛ ዲግሪ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው ዕጩ ዶ/ር አዲሱ አዳሙ የምርምር ሥራውን ሰኔ 23/2015 ዓ/ም የውስጥና የውጪ ገምጋሚዎች በተገኙበት አቅርቧል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የመመረቂያ ጽሑፉ ‹‹English Language Teachers’ Awareness, Self-Efficacy Beliefs and Class Room Practices of Task - Based English Language Teaching in Teaching Speaking Skills: Selected Gamo Zone Secondary School Teachers in Focus›› በሚል ርዕስ የተከናወነ ሲሆን ጥናታዊ ጽሑፉም አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡

ዕጩ ዶ/ር አዲሱ የመጀመሪያ እና 2ኛ ዲግሪውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማግኘት በጨንቻ እና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ ግንኙነት እና በመምህርነት ያገለገለ ሲሆን በ2011 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባገኘው የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቷል፡፡

ዕጩ ዶ/ር አዲሱ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመናገር፣ የመጻፍና የማንበብ አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው የመምህራን የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴ በተሻሻለ ቁጥር የተማሪዎች የቋንቋ አቅም የሚያድግ በመሆኑ ጥናታቸው ለተማሪዎች ሥራን በመስጠት ሥራውን በመሥራት ውስጥ ቋንቋን እንዲማሩ በሚያበረታታ የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴ ላይ ማተኮሩን ገልጿል፡፡

በግምገማ መርሃ ግብሩ ዶ/ር ኃይሉ ውብሸት ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና ዶ/ር ይናገር ተክለሥላሴ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በውጪ ገምጋሚነት፣ ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውስጥ ገምጋሚነት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ዕጩ ዶ/ር አዲሱ የዶክትሬት ዲግሪው በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ከጸደቀ በኋላ የሚያገኝ ይሆናል፡፡    

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት