አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ2015 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ሙከራ (Model Exit-Exam) ሰኔ 23/2015 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደተናገሩት ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ሙከራ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ሲሆን የመውጫ ፈተና ልምምዱ በተማሪዎች በኩል የምሥጢር ቁጥር መሸምደድና መቀየር፣ የኮምፒውተር አጠቃቀም፣ በትምህርት ያገኙት ዕውቀት ምን ያህል እንደሆነ መለየት እና የመሳሰሉ ጉዳዮችን እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኢንተርኔትና ኮምፒውተር ዝግጅቶች በትክክል መተግበራቸውን ለመለየት የሚረዳና ዩኒቨርሲቲው ሀገር አቀፉን የመውጫ ፈተና ማካሄድ እንደሚችል ያሳየ ነው፡፡ ፈተናው ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች የያዘና ተማሪዎች አቅማቸውን የሚያዩበት እንደሆነም ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ክትትል፣ ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ እንደገለጹት በትምህርት ሚኒስቴር ጸድቆ ስለተላከው የመውጫ ፈተና መመሪያ ማስፈጸሚያ ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡

ለመውጫ ፈተና ዝግጅት በትምህርት ሚኒስቴር የተለየውን የትምህርት ክፍሉ ኮርሶች ዋና የብቃት መለኪያ ይዘት /Core Competence/ ለእያንዳንዱ ተማሪ እንዲደርስ በማድረግ እንዲሁም የሙከራ ፈተናዎች በወረቀትና በበይነ መረብ በመስጠት ፈተናውን በኢንተርኔት ሲፈተኑ አዲስ እንዳይሆንባቸው ለበርካታ ጊዜ ልምምድ ማድረጋቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ሠረቀብርሃን ተማሪዎች በተሟላ ደረጃ ለዋናው መውጫ ፈተና ራሳቸውን በሥነ-ልቦና፣ በዕውቀትና በክሂሎት እንዲያዘጋጁ የማረጋገጥ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የመውጫ ፈተና ሙከራው በዩኒቨርሲቲው በ65 የትምህርት ፕሮግራሞች ለ3,195 ተመራቂ ተማሪዎች እንዲሁም ከግል ኮሌጆች በ10 የትምህርት ፕሮግራሞች ተሰጥቷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው 5ኛ ዓመት የሶፍትዌር ምኅንድስና ተማሪዎች ዕጹብ ያዕቆብ እና ገመችስ ከድር በሰጡት አስተያየት በሙከራ ፈተናው በአምስት ዓመት ቆይታቸው ምን ያህል እንዳወቁና ለሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተናው ምን ያህል እንደተዘጋጁ ራሳቸውን የፈተሹበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሙከራ ፈተናው ወቅት የገጠማቸው የኢንተርኔት ኮኔክሽን ችግር በሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተናው ላይ እንዳይከሰት ከወዲሁ ቢታሰብበት መልካም ነውም ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት