በ2015 ዓ/ም ለሚመረቁ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሁም ለዳግም ፈተና ወሳጆች ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና እና የሙያ ፈቃድ ምዘናን አስመልክቶ ሰኔ 29/2015 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በጤና ሚኒስቴር የጤና ተቋማትና የጤና ነክ ቁጥጥር ባለሙያና የፈተናው ሱፐርቫይዘር አቶ አሰግድ በቀለ እንደተናገሩት የመውጫ ፈተናው በትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በተመሳሳይ ሰዓት በበይነ መረብ የሚሰጥ በመሆኑ ተማሪዎች ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎችንና ግዴታዎቻቸውን እንዲያውቁ ገለጻው አስፈልጓል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎች አስቀድመው በቂ ዝግጅት በማድረግና ችግሮች ቢከሰቱ በአስቸኳይ በመቅረፍ ተማሪዎችን ለፈተናው ዝግጁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰሎሞን ንዋይ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በመውጫ ፈተና ዙሪያ የተለያዩ ግብዓቶችን እያዘጋጀና ተማሪዎች በሥነ-ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የመውጫ ፈተናው ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ዓመት ከወሰዱት ኮርስ መካከል መሠረታዊ ከሚባሉ 15 ኮርሶች የሚዘጋጅ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ትምህርት ክፍሎችም መሠረታዊ ኮርሶችን በመለየት ተማሪዎቻቸውን በዕውቀት፣ በክሂሎትና በአመለካከት ብቁ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥያቄዎችን ሲያዘጋጁ ቆይተዋል፡፡ ገለጻው አጠቃላይ ፈተናው ምን እንደሚመስልና ከተማሪዎች የሚጠበቁ ጉዳዮችን አስመልክቶ መሰጠቱን ዶ/ር ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ የኮምፒውተር አጠቃቀም ክሂሎት ክፍተት ያለባቸው ተፈታኞች በጠየቁት ጥያቄ መሠረት ለተወሰኑ ተፈታኞች ማሳያ ተደርጓል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት