የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ዐጸደ ሕፃናት ት/ቤት የወላጅ በዓል ሐምሌ 01/2015 ዓ/ም በድምቀት ተከብሯል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ወላጆች በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ለልጆቻቸው የሚያደርጉት እንክብካቤ የሕፃናቱን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን መሆኑንና ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ይልቅ ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው ወላጆች ጤንነታቸውንና ደኅንነታቸውን መጠበቅ፣ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ እንዲሁም ሕፃናቱ ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮችንና ማኅበራዊ እሴቶችን እንዲለዩ ማስቻል ከጥሩ ወላጆች የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተክሉ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ለሕፃናት ቀጣይ ሕይወት መሠረት የሚጣልበት እና ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው ዝግጁ የሚሆኑበት በመሆኑ ወላጆች ለተማሪዎቹ ውጤት እና ሥነ-ምግባር መሻሻል ከት/ቤቱ አመራር አካላት ጋር በጥምረት ሊሠሩ ይገባል፡፡

የኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና በሪፖርታቸው እንደገለጹት በኮሚዩኒቲ ዐጸደ ሕፃናት ት/ቤት በ2015 የትምህርት ዘመን የማቆያ ሕፃናትን ጨምሮ 203 ወንድ እና 198 ሴት በድምሩ 401 ሕፃናት የተመዘገቡ ሲሆን ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው በዓመቱ መጨረሻ የተዘጋጀውን ፈተና ከወሰዱ 392 ተማሪዎች 364ቱ ከ75 በመቶ በላይ ውጤት በማስመዝገባቸው የትምህርቱን አፈጻጸም ስኬታማ እንዲሆን አስችሏል፡፡

በትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሥራ በወቅቱ መጀመሩ፣ የመማሪያ መጻሕፍትን ለማሟላት ጥረት መደረጉ፣ የሕጻናቱን ውጤትና ሥነ-ምግባር መሻሻል የሚገልጽ ፖርትፎሊዮ/የክትትል መዝገብ/ መዘጋጀቱ እንዲሁም የመምህራንን ሙያ ለማሻሻል የሚያግዙ ሥልጠናዎች መሰጠታቸው ጠንካራ አፈጻጸም ሆነው ተመዝግበዋል፡፡

በአንጻሩ ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ግንባታዎች መስተጓጎል እና የት/ቤቱ የቅበላ አቅም ከወላጆች የማስመዝገብ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አለመሆን ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸው እንዲሁም በትምህርት ዘመኑ የታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በፕሮግራሙ ግጥም፣ ራስን ማስተዋወቅ፣ ጭውውት እንዲሁም የተለያዩ ትዕይንቶች በሕፃናቱ ቀርበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት