‹‹ነገን ዛሬ እንትከል!›› በሚል መሪ ቃል 5ኛው ዙር ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 10/2015 ዓ/ም ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ ሁሉንም የዩኒቨርሲቲውንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ ይጀመራል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

እንደ ሀገር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ መያዙን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ችግኞችን አዘጋጅቶ ለማኅበረሰቡ የማሰራጨት፣ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢና አካባቢው የመትከል እና የመንከባከብ ሥራዎችን መደበኛ ዓመታዊ የሥራ አካል በማድረግ በትኩረት ሲሠራ መቆየቱንና በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግኞችን የመትከል፣ የመንከባከብ እና የመጠበቅ ባህሉን እያሳደገ እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማካሄድ በዩኒቨርሲቲው በኩል በቂ ዝግጅት የተደረገ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማኅበረሰብ በጋራ በመሆን በአቅራቢያ ባሉ ተፋሰሶችና ካምፓሶች ችግኞችን በመትከል አሻራውን እንዲያኖር ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

እንደ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ በጀት በማውጣት ከአካባቢው የአየር ሁኔታ ጋር የሚሄዱ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞች የተዘጋጁ መሆናቸውን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ችግኞችን መትከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በዕለቱ በነቂስ ወጥቶ በተዘጋጀው የመትከያ ሥፍራ ላይ ችግኝ በመትከል የአካባቢውን ሥነ-ምኅዳር የመጠበቅ ድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በዘጠኙ የችግኝ ጣቢያዎች የሚሠራጩና የሚተከሉ በአማካይ እስከ 1 ሚሊየን የሚደርሱ ከ15 በላይ ዝርያ ያላቸው ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን በዕለቱም በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ብቻ 10 ሺህ ችግኞች በኮንሶ መሄጃ መንገድ ከሼቻ ቁልቁለት ወረድ ብሎ ባለው አካባቢ ጠዋት ከ12፡00 ጀምሮ የተፋሰስ ዛፎች ተከላ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ካምፓሶች ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬና የውበት ዛፎችን በራሳቸው መርሃ ግብር እንደሚተከሉ ዶ/ር ተክሉ አሳውቀዋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግና የሚተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እንክብካቤ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ በመርሃ ግብር ላይም ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንዲሳተፍ ዳይሬክተሩ በአጽንኦት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
v