በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 7/2015 ዓ/ም ድረስ ሲሰጥ የነበረው የ2015 ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና/Exit –Exam/ በስኬት ተጠናቀቀ፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የመውጫ ፈተናው ለዩኒቨርሲቲው ተመራቂ ተማሪዎችና ከግል ኮሌጆች ለተወጣጡ ተፈታኞች ሲሰጥ የቆየው ፈተና አጠቃላይ ሂደት በበቂ ዝግጅትና ጥብቅ ክትትል መመራቱ ሥራው በስኬት እንዲጠናቀቅ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ የብቃት መለኪያ ምዘናዎች የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንፃር ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዝደንቱ በዋናነት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተገቢውን ዕውቀትና ክሂሎት ማግኘታቸውን ለመፈተሸ ይጠቅማሉ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በተቋማት መካከል የውድድር መንፈስና መነሳሳትን ለመፍጠር እንዲሁም በተማሪዎች የሚመዘገብ ውጤትን መሠረት በማድረግ የግብዓት፣ የመማር ማስተማር ሥነ-ዘዴ እንዲሁም የሥርዓተ-ትምህርት ማሻሻያዎችን ለማድረግ መሰል የምዘና ፈተናዎች ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ዶ/ር ዳምጠው ጠቁመዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ለ2015 ተመራቂ ተማሪዎች በኦንላይን የተሰጠው የመውጫ ፈተና በዚህ ልክ ሲሰጥ የመጀመሪያ ልምድ እንደመሆኑ ያጋጠሙ ፈታኝ ሁኔታዎችን በከፍተኛ ርብርብና ትጋት በማስተካከል ፈተናውን በስኬታ ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የራሱን 3199 ምሩቃን እንዲሁም ከግል ኮሌጆች የተመደቡ ሌሎች ተፈታኝ ምሩቃንን ጨምሮ 6,899 ተማሪዎች እንዲያስፈትን በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለት ሲሆን ከእነዚህም መካከል 6,109 ፈተናውን መውሰዳቸውን ዶ/ር ዓለማየሁ ጠቁመዋል፡፡ ዶ/ር ዓለማየሁ አጠቃላይ የፈተናው ሂደት በዚህ መጠን በስኬት እንዲጠናቀቅ የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችና የሚኒስቴሩ ኢኖፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቡድን ያለምንም መታከት ሲያደርጉት የቆዩት ድጋፍ ወሳኝ ሚና የነበረው ሲሆን በዩኒቨርሲቲያችን የሚገኙ የኢንስቲትዩት፣ የካምፓስ፣ የኮሌጅና የትምህርት ቤት ኃላፊዎች ያሳዩት ትጋትና ቁርጠኝነት ለዚህ ሀገራዊ ተልዕኮ በስኬት መጠናቀቅ ጉልህ ሚና ያበረከቱ በመሆኑ ያላቸውን ልባዊ አድናቆትና ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ዘርፍ ለፈተናው የሚያግዙ የሎጂስቲክ አቅርቦት ሥራዎችን ሲመራና ሲያስተባብር የቆየ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም የአይሲቲ/ICT/ እና የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ግብዓቶችን ማሟላትና ለፈተናው ዝግጁ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ በስፋት ተሠርቷል ብለዋል፡፡ ፈተናውን በኦንላይን ለመስጠት የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶችን በበቂ ሁኔታ ማሟላት መቻሉ ፈተናውን ያለምንም መቆራረጥና ችግር ማጠናቀቅ እንዲቻል ጉልህ ሚና ያበረከተ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቷ ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ ታሪኳ ኢትዩ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት፣ የዩኒቨርሲቲው የአይሲቲ/ICT/ ባለሙያዎች፣ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም የዞንና የከተማ ፀጥታ መዋቅር ለፈተናው በስኬት መጠናቀቅ የጎላ ሚና የተጫወቱ መሆናቸውን በመጥቀስ ለዚህም በዩኒቨርሲቲው ስም ያላቸውን ልባዊ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ላለፉት 6 ቀናት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለቆዩ ምሩቃን በዩኒቨርሲቲው ሲሰጥ በቆየው ፈተና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ጨምሮ ከሳታ፣ ፓራሚድ፣ መካነኢየሱስ፣ አልያንስ፣ ዳሞታ፣ አትላስ፣ ጎፋ ዩኒቨርሳል፣ ኒው ግሎባልና ሌሎች የግል ኮሌጆች ምሩቃን ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት