አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የሕግ ት/ቤት እንዲሁም የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የሳውላ ካምፓስ ተማሪዎችን እንዲሁም በሁሉም ኮሌጆችና ፕሮግራሞች በ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ሐሙስ ሐምሌ 13/2015 ዓ/ም በዋናው ግቢ አዲሱ አዳራሽ እና ዓርብ ሐምሌ 14/2015 ዓ/ም በሳውላ ካምፓስ  በደማቅ ሁኔታ የሚያስመርቅ ይሆናል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮውን ተመራቂዎች ቁጥር ሳይጨምር ባለፉት 35 ዙሮች ከ72 ሺህ በላይ ምሩቃንን በማፍራት በሀገራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ተቋማት በከፍተኛ የሙያ ብቃት አሻራቸውን የሚያሳርፉ ምሁራንንና ባለሙያዎችን በማሠልጠን የበኩሉን ድርሻ በትጋት እየተወጣ የሚገኝ አንጋፋና ስመ ጥር ተቋም ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለ2015 ዓ/ም ምሩቃንና ቤተሰቦች በጉጉት ስትጠብቋት ለነበራችኋትና ይሂችንም ዕለት በስኬት ለመድረስ በቅንጅትና በትጋት ስትሠሩ የነበራችሁበትን የድካምና ልፋት ውጤት ለምታዩባት ዕለት እንኳን አደራሳችሁ፤ እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቱን ከወዲሁ ያስተላልፋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት