በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የብዝኃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ከእምቦጭና ፓርቲኒየም አረሞች ብስባሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (Compost) በመሥራት የበቆሎ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡  ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ሽቴ ጋተው መድኃኒትነት ያላቸው፣ ሊጠፉ የተቃረቡና የምግብ ዋስትናን ለማረጋጥ የሚያግዙ ዕፅዋትን ለትውልድ ለማስተላለፍ ምርምርና ጥበቃ ማካሄድ የማዕከሉ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸው እምቦጭን ከዓባያ ሐይቅ እና ፓርቲኒየምን ከየማሳው በመውሰድና ሁለቱን አበስብሶ በማዋሐድ በግዥ የሚገኙትን ዩሪያና ዳፕ ማዳበሪያዎች ሊተካ የሚችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመሥራት ማዕከሉ ምርምር እያካሄደ ነው ብለዋል፡፡

መጤ አረሞች አፈር፣ ሐይቆችና የሐይቅ ብዝሃ ሕይወትን እንደሚያጠቁ የገለጹት ዶ/ር ሽቴ የምርምር ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ጎጂ አረሞችን ጥቅም ላይ ማዋል፣ ውጤታማነታቸውን ደጋግሞ ማረጋገጥና ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ አስጨብጦ ማዳበሪያውን ማዳረስ ቀጣይ ሥራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ አቶ አታላይ አዘነ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አሠራር ሂደቱን አስመልክቶ ሲያብራሩ እምቦጭና ፓርቲኒየም አረሞች አበባና ፍሬ ከማውጣታቸው በፊት ተሰብስበው ተገቢውን ሕክምና በማድረግ 50 በመቶ ፓርቲኒየምና 50 በመቶ እምቦጭ በማዋሐድ የከብቶች እዳሪ በመጨመር ተቀብሮ ለ60 ቀናት እንዲቆይ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በዚህ መልኩ የተዘጋጀውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ መልካሳና ፖይነር የበቆሎ ዝርያዎችን አብሮ በመዝራት በ20፣ 40ና 60 ቀን የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በመጨመር በአበቃቀል፣ እድገትና ምርታማነት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ካልተጨመረበት በቆሎ ልዩነት እንዳለው ለማየት መቻሉን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ምርቱ ጥሩ ጣዕም ያለው፣ ለመታኘክ የማያስቸግርና ለጤና ተስማሚ መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው ጣዕሙን፣ ሽታውንና ያለውን ለውጥ አስመልክቶ ግብረ መልስ ለማግኘት በማዳበሪያ የተመረተውን እሸት በቆሎ ያለ ማዳበሪያ ከተመረተው በምሥጢር ጽሑፍ (በኮድ) በመለየት ለተወሰኑ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

እሸት በቆሎው ከደረሳቸው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት እንደገለጹት በቆሎዎቹ B1 m-T3 R3 እና B2 m-T0R2 የሚሉ በወረቀት ላይ የተጻፉ ኮዶች ያላቸው ሲሆን B2 m-T0R2 ኮድ ያለበት በቆሎ ወፍራም ፍሬና ጥሩ መዓዛ ያለው ሲሆን ይህም ኮድ በተፈጥሮ ማዳበሪያ የተመረተው በቆሎ መለያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት