የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ሙሉ 1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የወላጅ በዓል ሐምሌ 08/2015 ዓ/ም ተከብሯል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት  የትምህርት ቤቶች ብቃት የሚለካው የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች በዕውቀት፣ በክሂሎትና በሥነ ምግባር የተሻሉ በማድረግ ከአንደኛው ክፍል ወደ ቀጣዩ ክፍል ማሻገር ሲችሉ ነው፡፡ ቀጣዩ የትምህርት ዘመን ስኬታማ እንዲሆን ወላጆች ከመምህራንና ከት/ቤቱ አመራር አካላት ጋር በጥምረት ሊሠሩ ይገባል ያሉት ፕሬዝደንቱ ስኬታማ መማር ማስተማር እንዲኖር ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ትምህርት የሁለትዮሽ ሥራ በመሆኑ ወላጆች ከት/ቤቶቹ ጋር ቅንጅታዊ ሥራ በመሥራት የልጆቻቸውን ውጤት፣ ሥነ ምግባርና የት/ቤቶችን ሁለንተናዊ ሁኔታ በመረዳት መልካም ወላጅ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገላጻ በ2014 የትምህርት ዘመን በኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 106 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 31 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ሲሆን የመግቢያ መስፈርት ከነበረው 700 ውጤት አንድ ተማሪ 629 ነጥብ በማምጣት በት/ቤቱ የመጀመሪያ፣ በክልል ደረጃ ሁለተኛ እንዲሁም በሀገር ደረጃ 10ኛ በመሆን አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ባላፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር ደረጃ በትምህርቱ ዘርፍ ከተስተዋሉት ተግዳሮቶች አንጻር በት/ቤቱ የተመዘገበው ውጤት የተሻለ እንደነበርም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ዞናዊ ፈተና ከወሰዱ 96 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በዞኑ ተሸላሚ ከነበሩት 3 ተማሪዎች 2ቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ተማሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ትምህርት የሰዎችን ሰብእና የሚገነባ፣ አእምሯዊ ጥንካሬ የሚያዳብርና ስኬታማ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት የኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና ት/ቤቶቹ ባስመዘገቡት ስኬታማ የመማር ማስተማር ተግባር የደረጃ ለውጥ ማምጣታቸው፣ የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት መኖሩ እንዲሁም የክፍለ ጊዜያት ብክነት ሳይኖር ተማሪዎች መማር የሚገባቸውን የትምህርት ይዘት ማግኘት መቻላቸው በትምህርት ዘመኑ ስኬታማ አፈጻጸም ሆነው መመዝገባቸውን በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የትምህርት ቤቱ መምህራን፣ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች የተገኙ ሲሆን ግጥም፣ መነባንብና ሌሎችም ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች በተማሪዎች ቀርበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት