አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን በድኅረ ምረቃ 3 ዲግሪ 12 እና 2 ዲግሪ 586 እንዲሁም በቅድመ ምረቃ 859 በአጠቃላይ 1,457 ተማሪዎችን ሐምሌ 13/2015 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 281ዱ ሴቶች ናቸው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የአስተዳደርና መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሰሎሞን አብርሃ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማሳካት የተደረገው ጥረት ውጤታማ ቢሆንም የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ የትምህርት ሥርዓቱ የገጠመውን ችግር ለማስወገድና የደረሰበትን ስብራት ለማከም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ቀርጾ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከመፍትሔዎቹ መካከል ዩኒቨርሲቲዎችን በትኩረትና በተልእኮ መለየት፣ የሥርዓተ ትምህርት ፍተሻ ማድረግ፣ የፈተና ሥርዓቱን ማዘመንና ማጠናከር፣ የመውጫ ፈተናን መተግበር፣ የአመራር ሥርዓቱን ማሻሻል እና ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ አገዝ ማድረግ ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

በተልእኮ ልየታው መሠረት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደ መሆኑ የልኅቀት ማዕከላቱን ማጠናከር፣ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የምርምር ቤተ ሙከራዎችን ማደራጀትና ችግር ፈቺ ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን መተግበር ላይ በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅበት ዶ/ር ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡ ምሩቃን ዕውቀት የማይከስር ሀብትና የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ በትምህርት ቆይታቸው ወቅት በንድፈ ሃሳብና በተግባር የቀሰሙትን ዕውቀት በሚሰማሩበት መስክ ሁሉ ለዘላቂ እድገትና ሽግግር እንዲጠቀሙ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተቋሙ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ካደገበት ከ1996 ዓ/ም ጀምሮ በልዩ ልዩ መስኮች የመምህራን ትምህርትና ሥልጠናን ጨምሮ ምሁራንን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው እስከ አሁንም የዛሬዎቹን 36 ዙር ተመራቂዎች ጨምሮ ከ77 ሺህ በላይ ምሩቃን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ የትምህርትና የምርምር ጥራትን ለማሳደግ ከመምህራን ልማት ባሻገር የማስተማሪያና የምርምር ቤተ ሙከራዎችንና ሠርቶ ማሳያዎችን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው የሚያስገነባው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታው እየተጠናቀቀና አስፈላጊ ቁሳቁሶች እየተሟሉለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን /አልሙናይ/ ማኅበር ጸሐፊ ጋዜጠኛ ሣልሳዊት ባይነሳኝ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለገጠሟት ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ለመሆን ምሩቃን በየተሰማሩበት የሥራ ዘርፍና በየደረሱበት አካባቢ ሁሉ በዕውቀትና በመልካም ምግባር እንዲያገለግሉ አደራ ብለው ምሩቃን የኅብረቱ አባል ሆነው ከሌሎች ምሩቃን ጋር እንዲሠሩና ለተማሩበት ዩኒቨርሲቲና ማኅበረሰብ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል ተማሪ አሸናፊ ኃይሉ ከውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3.94፣ ተማሪ ሀብታሙ ኩጫሮ ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3.95፣ ተማሪ ኢያሱ ካሳ ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 3.97 እና ተማሪ በሱፈቃድ ታደሰ ከሕግ ት/ቤት 3.92 በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ከአጠቃላይ ሴት ተመራቂዎች ተማሪ ኤደን አማረ ከውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3.9፣ ተማሪ ትዕግሥት አማከለው ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 3.92 እና ተማሪ ሃና ፍሬስብሃት ከሕግ ትምህርት ቤት 3.55 በማምጣት ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሬጂስትራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ እና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ተመራቂ ተማሪዎችን ለምረቃ ያቀረቡ ሲሆን የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም የምረቃ መርሃ ግብሩን መርተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት