በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የ2015 ትምህርት ዘመን ሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መርሃ ግብር ከነሐሴ 19-20/2015 ዓ/ም የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች፣ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝደንቶችና አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝደንቶች በተገኙበት በአርባ ምንጭ ከተማ ኃይሌ ሪዞርት ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለጹት ባለፉት አምስት ዓመታት ዋና የትምህርት ሴክተሩ ቁልፍ ችግር ተብሎ የተለየው የትምህርት ጥራትና ተገቢነት ጉዳይ ሲሆን ይህንንም ለማሻሻል በሪፎርም መልክ የሚተገበር የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀና የዩኒቨርሲቲዎችን የትምህርት ቆይታ ጊዜ ከሦስት ወደ አራት ዓመት የማሳደግ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን በትኩረትና በተልዕኮ የመለየት፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚደረገውን የመግቢያ ፈተና ጥራት ማስተካከል፣ ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ የመውጫ ፈተናን መተግበር፣ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት የመዘርጋትና አዋጁን የማጽደቅ እንዲሁም ተያያዥ የሆኑ ተጨማሪ የሪፎርም ሥራዎች ጥራት ላይ ማተኮር እና የውስጥ ግብዓቶችን ማሻሻል ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡  

ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም በ2016 የትምህርት ዘመን የተጀመሩ ሪፎርሞችን መሬት የማስያዝ፣ ባህል የማድረግና የማዝለቅ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን የመለየትና በተለዩበት ፕሮግራም ላይ ብቻ ተማሪ እንዲቀበሉና ፕሮግራሞችን ኦዲት እንዲያደርጉ የማድረግ፣ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ተፈትነው እንዲገቡና በድኅረ ምረቃ ትምህርት ጥራት ላይ ያለውን ጉድለት የማረም፣ የተሻለ የመውጫ ፈተና ለድጋሚ ተፈታኞችና ለመደበኛ ተማሪዎች የመስጠት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ የማድረግ፣ የትምህርት መሠረተ ልማትና ግብዓቶች እንዲሟሉና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዘላለም አሰፋ ባቀረቡት ሠነድ ከኮቪድ በኋላ ዓለም ላይ ያሉ 49% ተማሪዎች ወደ ኦንላይን መማር ማስተማር እየሄዱ በመሆኑ ካምፓስ ገብቶ የሚሰጠው የመማር ማስተማር ሂደት ወደ ኋላ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡  የሌላው ዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየው የኦንላይን ትምህርት ዜጎች ባሉበት ቦታ ሥራቸውን እየሠሩ ማንኛውንም ትምህርት መማርና ራሳቸውን ማሳደግ የሚችሉበት ቢሆንም  በኢትዮጵያ ባሉ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት በኦንላይን መማር ማስተማር እየተካሄደ አይደለም ብለዋል፡፡   

ዶ/ር ዘላለም አክለውም በሀገራችን በዲጂታል መማር ማስተማር ላይ ምንም የተሠራ ሥራ አለመኖሩንና ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ፈጥነው ወደ ሥርዓቱ መግባት እንዳለባቸው ገልጸው በተያዘው የአምስት ዓመት ዕቅድ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተወሰኑትን ፕሮግራሞች ሙሉ በሙሉ በኦላይን/Online/፣ የተወሰኑትን ደግሞ ከፊል በኣካልና ከፊል በኦንላይን/Blending/  አማራጮች ጭምር ማስተማር እንዲችሉ የሚሠራ ሲሆን ለዚህም ዝግጅት አምስት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተመርጠው የመርጃ ቋት/Resource Center/ እንደሚያደራጁ ተናግረዋል፡፡ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሰው ሀብት ልማቱን በቴክኖሎጂ መደገፍ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትን መጨመር በመሆኑ ከስትራቴጂው ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የዲጂታል ክህሎትን ለመገንባት ለዩኒቨርሲቲዎች የአሠልጣኖች ሥልጠና እየተሰጠ እንዳለና በቀጣይም ሥልጠናው ለሁሉም የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብና በአካባቢው ላሉ 2 ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመስጠት በቀጣይ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመክፈት እንሠራለን ብለዋል፡፡

ሻያሾኔ/SHAYASHONE (SYS) የተሰኘ ኃላፊነቱ የተወሰነ በግብርናና በግብርና ንግድ ላይ የተሻለ ተሞክሮ ያለው የግል ድርጅት በአሁን ሰዓት ወደ ትምህርት ሴክተርም በመግባት በe-SHE/e-Learning for Strengthening Higher Education/ ፕሮጀክት የኦንላይን ትምህርት የመርጃ ቋት ለማቋቋም ከትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ እና ከተመረጡ ከአዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመሥራት የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሠነድ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

በፕሮግራሙም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች፣ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቶችና አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝደንቶች እንዲሁም ለተጋባዥ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የምርምር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያምም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን፣ አርባ ምንጭ ከተማንና አካባቢዋን አስተዋውቀዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

 የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት