የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በ“AMU-IUC” ፕሮግራምና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በጫሞ ሐይቅ ዳርቻ ረግረጋማ ስፍራ ላይ የምርምር ውጤትን መሠረት በማድረግ እየተከናወነ የሚገኘውን የመልሶ ማልማት ሙከራ /Pilot/ ሥራን ነሐሴ 13/2015 ዓ/ም ጎብኝተዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በሐይቁ ዳርቻ ላይ ተሠርቶ የተመለከቱት መልሶ የማልማት ሙከራ ሥራ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ገልጸው በዋናነት ሥራው ጥናትና ምርምርን መሠረት በማድረግ እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም አንድምታው ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል፡፡ የመልሶ ማልማት ሥራው ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባሻገር ለአካባቢው ወጣቶች አመራጭ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ያሉት ፕሬዝደንቱ ከዚህም ባሻገር ቦታው በዘርፉ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች ዕውቀትና ልምድ የሚቀስሙበት ሠርቶ ማሳያ ሊሆን እንደሚችልም በምልከታቸው መገንዘባቸውን አመላክተዋል፡፡ የተጀመረው ሥራ ለቀጣይ ሰፋፊ በመስኩ ለመሥራት ለታሰቡ ሥራዎች መነሻና ልምድ እንደሚሆን የገለጹት ዶ/ር ዳምጠው መሰል ሥራዎችን ለማስፋትና በፕሮጀክቱ ለማከናወን ለታቀዱ ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው ቅድሚያ ሰጥቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው በሁለቱ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ላይ ምርምሮችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው በተለይ በጫሞ ሐይቅ ዳርቻ ላይ በአካባቢው በዓሣ ማስገር ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኙ የሚያስችሉ ተግባራትን ባቀናጀ መልኩ እየተከናወነ የሚገኘው መልሶ የማልማት ሥራ የምርምር ውጤቶች በተግባር የተቀየሩበት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የመስክ ምርምር ሠርቶ ማሳያ መፍጠር ያስቻለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከሶስት ወራት በፊት ስፍራውን እንደጎበኙና በወቅቱም ቦታው ገላጣ መሬት እንደነበር ያስታወሱት ም/ፕሬዝደንቱ አሁን ላይ ባዩት ተጨባጭ ለውጥ በእጅጉ እንደኮሩና በቀጣይ እንደ ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በዚህ ስፍራ የተገኘውን ዕውቀት የማስፋት ሥራ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን በበኩላቸው በስፍራው ላይ እየተከናወነ የሚገኘው መልሶ የማልማት ሥራ በዓሣ አስጋሪዎች ዘንድ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር ያስቻለ እንዲሁም ለአስጋሪዎቹ ተጨማሪ የገቢ አመራጭ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ ፋይዳው ከአካባቢና ተፈጥሮ ጥበቃ ባሻገር የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቷ በጉብኝታቸው ስፍራውን የማልማት ተግባር ከዩኒቨርሲቲው ተልዕኮዎች አንፃር እንዲሁም በቀጣይ በስፍራው ሊሠሩ የታሰቡ ሥራዎች አካባቢውን ብሎም ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ መሆናቸውን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው  በቀጣይ ሊሠራ ለታሰበው የግንባታ ሥራ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅብትን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የ“AMU-IUC” ፕሮግራም ማኔጀርና የውሃ ሥነ-ምኅዳር ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ  የመስክ ምልከታው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች የሐይቁ ማጣሪያ ኩላሊት የሆነውን ረግረጋማ ስፍራ መልሶ የማልማት ሥራን የእስከ አሁን አፈፃፀም በተግባር በማስመልከት በቀጣይ በስፍራው ላይ ለመሥራት ለታሰበው ተፈጥሮ ጋር የተስማማ መዝናኛ ስፍራ ግንባታ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ለማስቻል የተዘጋጀ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከወራት በፊት “AMU-IUC” እና የሌቶ ዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር በጋራ በመሆን የተረከቡት ይህ ሦስት ሄክታር  ረግረጋማ ስፍራ ከሰው ንኪኪ ነፃ እንዲሆን በማድረግ መልሶ የማልማት ሥነ-ሕይወታዊ ሥራዎች በመከናወናቸው ስፍራው ከዚህ ቀደም ወደ ነበረበት ሁኔታ እየተመለሰ ሲሆን በስፍራው ገቢ የሚያስገኙ ዕጽዋት ጭምር የተተከሉ በመሆኑ ለማኅበሩ ተጨማሪ የገቢ አማራጭ መፍጠር እየተቻለ መሆኑን ዶ/ር ፋሲል ጠቁመዋል፡፡ በሐይቁ ዳርቻ ላይ የዓሣ ማራቢያ ገንዳዎች ጭምር የተሠሩ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ፋሲል ይህም ለማኅበሩ ተጨማሪ የገቢ አማራጭ ከመፍጠሩ ባሻገር በሐይቁ ላይ የሚፈጠረውን ጫና በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ፋሲል አክለውም በአጠቃላይ በስፍራው ላይ እየተከናወነ ያለው ሥራ ተፈጥሮን በጠበቀ መልኩ ከእርሻ ባሻገር ያሉ ተግባራትን በማከናወን ማኅበረሰቡን በገቢ ረገድ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ማሳያ የሚሆን በመሆኑ በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ልምዱን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ እስከ 50 ሜትር በታረሱ የሐይቁ ረግረጋማ ስፍራዎች ላይ ለማስፋት ይሠራል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት