ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ AMU-IUC ፕሮግራም ፕሮጀክቶች አንዱ በሆነውና በጤናው ዘርፍ የእናቶችንና ሕፃናትን ጤና ለማሻሻል የሚተገበረው ፕሮጀክት የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር ውጤት የደረሰበትን ደረጃ የማስተዋወቂያ ወርክሾፕ ነሐሴ 18/2015 ዓ/ም ተካዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንትና የ‹‹AMU-IUC›› የምርምር ፕሮጀክቶች አስተባባሪ ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በ‹‹AMU-IUC›› ፕሮግራም ፕሮጀክት III የመጀመሪያ ዙር የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የምርምር ውጤታቸው የደረሰበትን ደረጃ ለኮሌጁ ማኅበረሰብና ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ ወርክሾፑ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ምርምሩ ለተካሄደበት ማኅበረሰብ ውጤቱን የማስተዋወቅ እንዲሁም ከሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ጋር የመነጋገር ሥራዎች እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አብነት ገ/ሚካኤል የፕሮጀክቱ የምርምር ሥራ የእናቶችና ሕፃናትን ጤና ለመንከባከብ እንዲሁም በሕክምና ዘርፍ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት ለመስጠት የሚጠቅም በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮግራም ፕሮጀክት III አስተባባሪና የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ አቶ ዋንዛሁን ጎዳና እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በመጀመሪያ ዙር ለአምስት ተማሪዎች የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል በመስጠት እያስተማረ ሲሆን ተማሪዎቹ በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ ተመርቀው ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ለምርምርና ለትምህርት የሚረዱ ቁሳቁሶችን በመግዛት ቤተ ሙከራ የማደራጀት ሥራ መሥራቱንም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ ከተገዙት ቁሳቁሶች መካከል ‹‹Bach Mixer›› ማሺን በምግብ ላይ ለሚሠሩ የግብርና ተመራማሪዎች እና በኅብረተሰብ ጤና ት/ከፍል ውስጥ በሥነ-ምግብና ጤና ላይ የሚያተኩሩ ጥናቶችን ከማጉላት አንጻር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አቶ ዋንዛሁን ጠቁመዋል፡፡

በወርክሾፑ ከቀረቡ ጥናታውዊ ጽሑፎች መካከል በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ት/ክፍል መምህርት መቅደስ ቆንዳሌ ‹‹Maternity waiting for Improved Institutional Delivery›› በሚል ርእስ የቀረበው ጥናት በአርባ ምንጭና ጋጮ ባባ ዙሪያ ወረዳዎች በተለያዩ ቀበሌያት የተካሄደ ሲሆን የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ 30 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ሄደው አይወልዱም፡፡ በዚህም አብዛኛው እናቶች በእርግዝና ወቅትና በወሊድ ጊዜ የሕክምና ባለሙያዎችን እርዳታ ስለማያገኙ ከወሊድ ጋር ለተያያዙ ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በሀገራችን የእናቶችን ከጤና ተቋማት ውጭ የመውለድ ምጣኔ ዜሮ ከመቶ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት መ/ርት መቅደስ ጥናቱ ይህን ዓላማ የሚደግፍ በመሆኑ ለአንድ ዓመት ባደረግነው የባለሙያ እገዛና በቪዲዮ የተደገፈ ትምህርት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ 10 ከመቶ ያህል መቀነስ አሳይቷል ብለዋል፡፡

በጋጮ ባባ ወረዳ ከመልክአ ምድሩ አቀማመጥ አንጻር የጤና ተቋዋማት ከማኅበረሰቡ ርቀው ስላሉ እናቶች ከመውለጃ ጊዜያቸው 15 ቀን ቀደም ብለው ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ በተዘጋጀላቸው የእናቶች መቆያ እንዲቆዩ ለማድረግ ተሞክሮ እንዳልተሳካ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በዘርፉ ጥናት የሚያደርጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አባወራዎችን ያሳተፈ ጥናት በማድረግ በእርግዝናና ወሊድ ወቅት ሊከሰት ከሚችል ሞትና ሌሎች ጉዳቶች እናቶችን እንዲታደጉ አሳስበዋል፡፡

በወርክሾፑ ከቀረቡ ጥናትና ምርምሮች መካከል ‹‹Iron and Vitamin A Sub-project››፣ ‹‹Innovative Video Based Health Education Sub-project››፣ ‹‹Maternity Waiting for Improved Institutional Delivery››፣ ‹‹Malaria and School Health›› እና ‹‹Cutaneous Leshimaniasis Sub-project›› የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በዕለቱ በፕሮጀክቱ አምስት ምርምሮች በተለይም በሁለቱ የደምና ሠገራ ናሙና ምርምራ ላይ ስላደረገው አስተዋጽኦ በኮሌጁ የሕክምና ላቦራቶሪ ሳይንስ ት/ክፍል የምስክር ወረቀት የተበረከተለት ሲሆን የት/ክፍሉ ተጠሪና የኮሌጁ የማኅ/ጉድ/ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ ረ/ፕ ገሊላ ቢረሳው የምስክር ወረቀቱን ተቀብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት