አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጀርመን ሀገር ከሚገኘው ዓለም አቀፍ ሮትራክት ድርጅት/Rotary Club Bonn International/ እና ሮተሪ ኢትዮጵያ/Rotary Ethiopia/ ጋር በመተባበር ‹‹Environmental Sustainability, Water and Agroforestry with Permaculture for Gircha in Ethiopia›› የተሰኘና ለሦስት ዓመታት የሚቆይ አዲስ የትብብር ፕሮጀክት በቆጎታ ወረዳ ነሐሴ 20/2015 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡ በግብርናና ደን፣ አፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ንጽሕናው የተጠበቀ የቤት አሠራርና አያያዝ እና የሶላር ፕላንቶች ጥገና ላይ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ በማኅበረሰቡ ቤቶች አስተማሪ ፖስተሮችን ማቅረብ እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ውጤቶች ዘላቂነት ትብብሮችን መመሥረት በፕሮጀክቱ ከሚተገበሩ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግርጫ ደጋ ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ከበደ ጆቢር እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም የ‹‹UNA_Village›› ፕሮጀክት ቡድን በኤዞና ጨንቻ ዙሪያ በመገኘት የማኅበረሰቡን አኗኗር ተዘዋውሮ ምልከታ ያደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ ኤዞ ቱላና ኤዞ ኦቴ ቀበሌያት ያለውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግና ማኅበረሰቡን አዲስ የአኗኗር ዘይቤ ለማስተማር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀበሌያቱ የግርጫ ምርምር ማዕከልን ለመገንባት የዋለውን መሬት በነፃ ለምርምር ሥራ ብለው በመስጠታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

የምርምርና ማኅ/ጉዳ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ‹‹UNA_Village›› ፕሮጀክት በተለያዩ ሀገራት የማኅበረሰቡን አጠቃላይ የግብርና፣ የኢኮኖሚ፣ የአካባቢ ጥበቃና የሥራ ዕድል ፈጠራን ማዕከል ባደረገ መልኩ የሚሠራ መሆኑን ገልጸው በቀበሌያቱ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ሥራዎች የሚሠሩበት እንዲሁም በግብርና ዙሪያ ያሉ እሳቤዎችና የአስተራረስ ዘዴዎች ተቀይረው ለአካባቢውም ሆነ ለሀገር አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው ብለዋል፡፡ የሀገራችን ዋና የኢኮኖሚ መዋቅር ግብርና ቢሆንም ሂደቱ ሳይዘምንና ምርታማነቱ ሳያድግ መቆየቱን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ ዕውቀትና ምርምርን ተጠቅሞ አስተራረስና ምርት አሰባሰብን በማዘመን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ቢሠራ ጠግቦ ከማደር ባሻገር ሀገሪቱ ለምታቅደው አጠቃላይ ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

እንደ ም/ፕሬዝደንቱ በዩኒቨርሲቲው ተጠቃሚውን ማኅበረሰብና የአካባቢውን ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በማስተባበር ጉልህ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን ሁለቱ ቀበሌያት ለዩኒቨርሲቲው ካሳዩት ተባባሪነት አንጻር ከዚህ ቀደም የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ ሁለት ትራንስፎርመሮች ተገዝተው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዮናስ ኡጎ እንደገለጹት ‹‹UNA_Village›› ፕሮጀክት ጀርመን ሀገር ከሚገኙ የበጎ አድራጎት ተቋማትና ረጂ ሰዎች፣ ከሮተሪ ክለብ ኢንተርናሽናል/Rotary Club Bonn International/ እና ከሮተሪ ኢትዮጵያ/Rotary Ethiopia/ ጋር በመተባበር የሚሠራ ሰፊ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ግብርና ላይ ትኩረት በማድረግ የከብት እርባታ፣ ለወጣቶች የሙያ ሥራ ሥልጠና፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች የተካተቱበት ነው፡፡ ምርምሩ በቆጎታ ወረዳ ሁለቱ ቀበሌያት የሚደረግ ሲሆን ለምርምር ሥራው የሚውል 5.4 ሚሊየን ብር በዋናነት በሮተሪ ክለብ ኢንተርናሽናል ጀርመኒ/Rotary Club International Germany/ እንደሚሸፈን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት በአካባቢው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና የመሬት ውስንነት ያለ መሆኑን እንዲሁም ወጣቶች በሥራ እጦት እንደሚቸገሩ ጠቁመው ተናግረው ፕሮጀክቱ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ማመቻቸት ላይ ቢሠራ መልካም መሆኑንና ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው ሥልጠና ባለው ውስን መሬት ለውጥ ማምጣት በሚቻልባቸው ዘዴዎች ላይ ትኩረት ቢያደርግ የሚረዳው ይሆናል ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ የወረዳው አስተዳዳሪና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት