የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ለሚገኙ ነርሶች፣ ጤና መኮንኖች፣ ሐኪሞችና የላቦራቶሪ ባለሙያዎች በቁንጭር (Cutaneous Leishmaniasis)ና ሌሎች የቆዳ በሽታዎች ዙሪያ ከነሐሴ 24/2015 ዓ/ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ


የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ታየ ቁንጭር በዞኑ በተለይም በዲታና ዳራማሎ ወረዳዎች በርካታ ሰዎችን እያጠቃና እየጨመረ ያለ በሽታ መሆኑን ገልጸው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ አዳዲስና ሥርጭታቸው የቆመ በሽታዎች እየተከሰቱ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ሌሽማኒያሲስ በተደጋጋሚ የተቸገሩበትና ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮ ጋር እየተነጋገሩበት የሚገኝ አሳሳቢ በሽታ ነው፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዞኑ በሕክምናው ዘርፍ የተለያዩ ትልልቅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ኃላፊው ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምር እና ሥልጠና ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ ዮሐንስ እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ትኩረት እያገኙ ሲሆን በጋሞ ዞንም ችግሮቹ ከመኖራቸው አንጻር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማዕከል አቋቁሞ ምርምሮችን፣ ሥልጠናዎችንና የተለያዩ ሀገር አቀፍ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡

ዳይሬክተሩ በጋሞ ዞን ዲታ፣ ዳራማሎና ዚጊቲ አካባቢዎች የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ከዞኑ በተጠየቀው መሠረት ሙያተኞችን በመላክ ለተወሰኑ ወራት ዳሰሳ ማድረጉንና የሕክምና ባለሙያዎች በዳራማሎና ዲታ ወረዳዎች ሕክምና ለመስጠት መሞከራቸውን ተናግረዋል፡፡ በበሽታዎቹ ዙሪያ በየአካባቢው ያሉ የጤና ባለሙያዎችና የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን ለማብቃት ሥልጠናው መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሕክምና ት/ቤት መምህርና በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የቆዳ ስፔሻሊስት የሆኑት አሠልጣኝ ዶ/ር ምሕረት ተጫነ የቦልቦ በሽታ ሕክምና አርባ ምንጭ ከተማ ላይ ብቻ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው ራቅ ባሉ አካባቢዎች ባሉ ጤና ተቋማት ሕክምናውን ለመስጠት በመታቀዱ በዳራማሎ፣ ጨንቻና ሰላምበር የጤና ባለሙያዎች ለመመርመርና በሽታውን ለማወቅ እንዲሁም ለማከም የሚያስችለውን ዕውቀት አግኝተው ዝግጁ እንዲሆኑ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ያለው የበሽታው ስፋት የብዙ ሴክተሮችን ርብርብ እንደሚፈልግ የተናገሩት ዶ/ር ምሕረት በዳራ ድሜና ጉጌ ባይራ አካባቢዎች ባደረጉት አሰሳ በአንድ ቀን ከ100 በላይ በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን ማግኘታቸውንና አብዛኛዎቹ ሕፃናት መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ምሕረት ከበሽታው ስፋት አንጻር የጤና ተቋቀማት ዝንጉነታቸውን በመተው ትኩረት መስጠት፣ በበሽታው መምጫና መከላከያ መንገዶች ላይ ወደ ማኅበረሰቡ በመውረድ ማሳወቅ፣ ሕክምናው የሚሰጥባቸው ተቋማትን ማቅረብ፣ መከላከያ መንገዶቹ ላይ የትብብር ጥናት ማድረግና የመሳሰሉት የመፍትሔ መንገዶች ናቸው፡፡

የቀድሞው ደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ኃይለኢየሱስ ተረፈ በጋሞ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ ቁንጭር በሽታ በስፋት መከሰቱንና ለረዥም ጊዜ ሆስፒታል ቆይተው ሕክምናውን ማግኘት ባለመቻላቸው ሕክምናውን ወደ ኅብረተሰቡ የማቅረብ ሥራ እንዲሠራ ከዞኑና ከወረዳው በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ቢሯቸው ጥያቄውን ለዓለም ጤና ድርጅትና ለጤና ሚኒስቴር በማቅረብ መድኃኒት በሆስፒታል ደረጃ ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ በየአካባቢያቸው የተጠቁ ሰዎችን እንዲያክሙ ለጨንቻና ሰላምበር ሆስፒታሎች መድኃኒት ማቅረባቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ኅብረተሰቡን በቅርበት ማገልገል እንዲቻል የባለሙያዎችን አቅም የሚገነባ ነውም ብለዋል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት