የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከ“Jhpiego Ethiopia Health Workforce Improvement Program” ጋር በመተባበር በደቡብ ኢትዮጵያ ለሚገኙ አምስት የጤና ሳይንስ ፕሮግራም ያሏቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፡- አርባ ምንጭ፣ ሀዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዋቸሞና ወልቂጤ እንዲሁም የአርባ ምንጭ እና ፋርማ የጤና  ሳይንስ ኮሌጆች ዓመታዊ የጤና ሳይንስ ትምህርት ጥራት ግምገማ ከነሐሴ 26-27/2015 ዓ/ም ድረስ አካሂዷል፡፡ ተጫማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት በአሁኑ ሰዓት የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት በተለይም ከጥራት አንጻር ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባለው የትምህርት ደረጃ  ጉልህ ክፍተት የሚስተዋልበት በመሆኑ ጥራቱን ለማስጠበቅ በመሠረታዊነት ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት፣ ጥራት ያለው የትምህርት ግብዓት እና ብቃት ያለው የአስተዳደር ሥርዓት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ጃፓይጎ ኢትዮጵያም በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በጤና ፕሮግራሞች አክሪዲቴሽን ሥራ ላይ የሰው ኃይል በማሠልጠን፣ ደረጃ እንዲዘጋጅ በማድረግ፣ ተገቢ የሆነ የተግባር ትምህርት እንዲሰጥ የሚያደርግ የቤተሙከራ አጠቃቀም ክሂሎት ድጋፍ በማድረግ ሥራው በአግባቡ እንዲሠራ አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ዓለማየሁ አክለውም ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ ከትምህርት አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ፈተና ድረስ በቴክኖሎጂ አስደግፎ መስጠት ወጪን ከመቀነሱም ባሻገር ሥራን በማቀላጠፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግና ለትምህርት ጥራትም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው  ጠቁመዋል፡፡ ቴክኖሎጂ በፈጣን ሁኔታ የሚለወጥ በመሆኑ በቀጣይ የበለጠ እንዲሠሩ እንዲሁም ጃፓይጎ ኢትዮጵያም ከኮሌጁ ጎን በመሆን እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡ ፕሮግራሙም የተጀመሩ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ በመገምገም እርስ በእርስ የምንማማርበት እንዲሁም ለቀጣይ የተሻለ ለመሥራት የሚታቀድበት ሊሆን እንደሚገባም ዶ/ር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

በ“Health Workforce Improvement Program” የደቡብ ኢትዮጵያ ኦፊስ ሪጂናል ማናጀር አቶ አስፋው ደምሴ እንደገለጹት የግምገማው ዓላማ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ሥራ ቀጣይነት ያለው እንደመሆኑ በተለይም የጤና ሳይንስ ተቋማት ያላቸውን አቅም በማጎልበት ከሥርዓተ ትምህርት፣ ከመምህራን አቅም ግንባታ፣ ከዲጂታላይዜሽን፣ ከተማሪዎች የፈተና አሰጣጥና ከተማሪዎች የተግባር ልምምድ ጋር በተያያዘ ያከናወኗቸውን ተግባራት ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲያዩና የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ተቋማት ተሞክሯቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በ2016 የትምህርት ዘመን በጤና ሳይንሱ ዘርፍ የትምህርት ጥራት በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሻሻል ትልቅ ግብዓትና አቅም ይዘው የሚሄዱበት መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡   

የሕክምናና ጤና ሳይንሱን ዘርፍ ስኬታማ ለማድረግ በኮሌጁ የተከናወኑ ተግባራትንና መልካም ተሞክሮዎችን ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መ/ር እና የተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ቢሮ አስተባባሪ አቶ አብነት ገ/ሚካኤል አዲስ እየተጀመረ ያለው የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ክትትልና ግምገማ ፕላትፎርም በየፕሮግራሙ ደረጃውን ጠብቆ የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት ዲጂታላይዝድ በሆነ መንገድ በይዘቱ ልክ መተግበር አለመተግበሩን ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን ይህም ፕላትፎርም በኮሌጁ የሙከራ ጊዜው የተጠናቀቀ ሲሆን በ2016 ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ፕላትፎርሙም የተቀላጠፈ የመማር ማስተማር ሥርዓት እንዲዘረጋ ክትትል በማድረግ ክፍተት ያለበትን ቦታ ለመለየትና ማስተካከያ ለማድረግ፣ ተማሪዎችም በቂ ዕውቀት ይዘው እንዲወጡ፣ የመውጫ ፈተናዎችንም በቀላሉ እንዲወጡ የሚረዳና የዩኒቨርሲቲውንም ገጽታ የሚገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መ/ር አብነት በኮሌጁ በኮምፒውተር በመታገዝ/Computer Based Testing/ ፈተናዎችን በኦንላይን እየፈተኑ እንዳሉና ይህም የትምህርት ግብዓቶችን ከማባከን በዘለለ ተማሪዎች ፈተናውን እንደተፈተኑ  ውጤታቸውን እንዲያውቁ የሚያደርግና ለመምህሩም ተማሪዎች ያልመለሷቸውን ጥያቄዎች የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የአርባ ምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መ/ርና የኮሌጁ የትምህርት ልማት ማኅበር አስተባባሪ መ/ርት ሰላምነሽ ተስፋዬ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ኮሌጁ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ሲሆን ከተማሪዎች ትግበራ ጋር ተያይዞ በመስክ ዙሪያ የተግባር ልምምድ፣ የመምህራን አቅም ማጎልበቻ፣ የኮሌጁን የውስጥ ጥራት አስመልክቶ በኅብረተሰብ ጤና፣ በሚድዋይፍሪ፣ በነርሲንግ፣ በፋርማሲና በላቦራቶሪ ዘርፍ ኦዲት መሠራቱንና ጥሩ ውጤትም መገኘቱን ገልጸዋል፡፡በተመሳሳዩም ወላይታ ሶዶ፣ ዋቸሞ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ፋርማ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያከናወኗቸውን ተግባራትና ጥሩ ተሞክሮዎች እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አቅርበው አፈጻጸማቸው ተገምግሟል፡፡

በትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራሚንግ ዴስክ ኃላፊ አቶ ዝናቡ አምሳሉ እንደገለጹት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለከፍተኛ ተቋማት ፈቃድ እና ዕውቅና /አክሪዲቴሽን/ የመስጠት፣ ጥራት ኦዲት የማድረግ፣  ተቋማት በተሰጣቸው ፈቃድና ዕውቅና ስለመሥራታቸው ቁጥጥር የማድረግ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በተጨማሪም ከሀገር ውስጥ የተገኙ የትምህርት ማስረጃዎችን የማረጋገጥ፣ ከሀገር ውጪ የተገኙ የትምህርት ማስረጃዎችን አቻ ግመታ የመሥራትና መሰል ተግባራትን እንደሚያከናውን ጠቁመዋል፡፡ ሁሉም ተቋማት ለተቋማቸውና ለፕሮግራሞቻቸው ዕውቅናን ለማግኘት ጥራትን ማስጠበቅና የተቀመጡ ደረጃዎችን አሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡ በዚህ መሠረት ተቋማትና ፕሮግራሞቻቸው ዕውቅና/አክሪዲቴሽን/ ከተሰጣቸው ዓለም አቀፍ ዕውቅና እና ተቀባይነትን እንደሚያገኙ፣ ተማሪዎች እና ኢንደስትሪዎች እንደሚመርጧቸው እንዲሁም መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን በልዩነት ሊያደርግላቸው እንደሚችል እና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ሊደግፋቸው ዝግጁ መሆኑን አቶ ዝናቡ ተናግረዋል፡፡  

የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ጃፓይጎ ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች ከተቋሙ ጎን በመሆን የሕክምናን ትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ እያበረከተ ያለው ድጋፍ በቀጣይ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያነሳሳና ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረው ድርጅቱ እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡  

በፕሮግራሙ  ከጃፓይጎ ኢትዮጵያ፣  ከትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከአምስት የተለያዩ የጤና ሳይንስ ፕሮግራሞች ካሏቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭና  ፋርማ ጤና ሳይንስ ኮሌጆች የመጡ አመራሮች፣ የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት