አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹International Bamboo and Rattan Organization/INBAR›› ከተሰኘና መቀመጫውን ቻይና ካደረገ ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የቆላ ቀርከሃ ችግኝ በማፍላት የዩኒቨርሲቲው፣ የድርጅቱ፣ የክልሉና የዞኑ አመራሮች በተገኙበት በላንቴ ኦቾሎ ቀበሌ ነሐሴ 25/2015 ዓ/ም የተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ ድርጅቱ ከሰጠው አንድ ኪሎ የቀርከሃ ዘር ውስጥ 15 ሺህ የሚሆኑትን ማፍላት የተቻለ ሲሆን በዕለቱ ስድስት በመቶ የሚሆኑት ችግኞች በላንቴ ኦቾሎ አካባቢ በዓባያ ሐይቅ ዳርቻ ላይ ተተክለዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎችንና የአፈር መሸርሸር የሚያጋጥማቸው ቦታዎችን ለማልማት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮችን እያካሄደና ችግኞችን በየወቅቱ እየተከታተለ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ ቀርከሃ የአፈር መሸርሸርን ከመከላከሉ ባለፈ ቤት ለመሥራትና የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶችን ለማዘጋጀት የሚጠቅም፣  ለወጣቶችና እናቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንዲሁም ለምግብነትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ሊውል የሚችል በመሆኑ በደጋው አካባቢ በስፋት እንደሚለማው ሁሉ በቆላ አካባቢም የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከ‹‹INBAR›› ጋር ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በትብብር እየሠራ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት አመራሮቹ በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በተጠናው መሠረት ዶርዜ አካባቢ ተገኝተው ከእንሰትና ቀርከሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ማኅበረሰቡ በተለይም ሴቶች የሚደርስባቸውን ልፋትና እንግልት ተመልክተዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ የእንሰትና የቀርከሃ ተክል በሚገኝባቸው አካባቢዎች በተለይም በገጠራማው ክፍል በድህነት የሚኖሩ ሴቶች ከተክሎቹ ጥቅም ለማግኘት የሚወስድባቸውን ጊዜ፣ የሚያወጡትን ጉልበትና የሚደርስባቸውን የሥራ ጫና ለመቀነስ ከዩኒቨርሲቲው በቀረበው ሃሳብ መሠረት ድርጅቱ በትብብር ለመሥራት መፈለጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ በጋሞ ዞን ወጣቶችን አደራጅቶ በማሠልጠንና የቀርከሃ ዘርን በመስጠት ችግኝ አፍልተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዳኘው ይበይን ድርጅታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በ50 ሀገራት በዋናነት በቀርከሃ አካባቢን በመጠበቅና የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚ በማሻሻል ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲመጣ የሚሠራ መሆኑንና በምሥራቅ አፍሪካ የድርጅታቸው ማዕከላዊ ቢሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዳኘው በዓለም ላይ ካሉ ከ1500 በላይ የቀርከሃ ዝርያዎች ውስጥ በኢትዮጵያ ሁለት የቆላና የደጋ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን በአፍሪካ 80 በመቶ የቀርከሃ ተክል ይዞታ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ድርጅታቸው በጋሞ ዞን ቦንኬ፣ ዲታና ሌሎች አካባቢዎች ለወጣቶችና አርሶ አደሮች በቀርከሃ አጠቃቀምና አያያዝ ላይ ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ማድረጉን የጠቆሙት አስተባባሪው በዚህም በቅርቡ በላንቴ ኦቾሎ ዓባያ ተፋሰስ ዙሪያ እንዲተከሉ 14 ሺህ የቀርከሃ ችግኞች መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው ደቡብ ክልል አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ዘርይሁን ዮሴፍ የደጋ ቀርከሃ እየጠፋ በመምጣቱና አዲስ ዝርያ መጀመር በማስፈለጉ የቆላውንና የደጋውን ቀርከሃ ለማብዛት እንደ ክልል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ አብርሃም አይካ ከዚህ ቀደም በዞኑ የቀርከሃ ዝርያዎች በደጋው አካባቢ በሰፊው ሲተከሉ መቆየታቸውንና ዘንድሮ የቆላ ቀርከሃ ተከላ እየተካሄደ መሆኑን አውስተው ቀርከሃን በቆላማው አካባቢ በማላመድ ውጤት ለማምጣት የዞኑ መንግሥት፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና INBAR ፕሮጀክት በባለቤትነት ክትትል ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት