አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ትራንስፎርሚንግ አግሪካልቸር(ETA) ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የእንሰት አመራረት ሂደትን የሚያሻሽሉ ዘመናዊ ማሽኖችን በማባዛት ለማኅበረሰቡ በስፋት በማዳረስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከግል ቴክኖሎጂ አምራች ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ውይይት ነሐሴ 23/2015 ዓ/ም  አካሂዷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት የውይይቱ ተሳታፊዎች የመስክ ምልከታ አድርገው በጋራ ለመሥራት ሙሉ ፈቃደኛ በመሆናቸው በቀጣይ የመግባቢያ ሰነድ ይፈረማል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ከእንሰት ምርት ጋር በተያያዘ የተሠሩት ቴክኖሎጂዎች ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ተቋሙ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ በሚዘጋጁ የመግባቢያ ሰነዶች ላይ በጋራ የሚሠሩት አካላት ድርሻዎች ተካተው እንደሚቀርቡና ውይይት እንደሚደረግባቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በውይይቱ በተነሱ ሃሳቦች መሠረት የእንሰት ማሽኖችን ማምረት ሂደት ላይ ማሻሻያዎችን ለማድረግና ጥሩ ተሞክሮዎችን አካቶ በጋራ ለመሥራት እንዲሁም ለአምራቾች፣ ለባለሙያዎች፣ ለአርሶ አደሮችና ለሚደራጁ ወጣቶች እንደ ተቋም ተከታታይነት ያለው የቴክኒክ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከምርት በኋላ የሚኖሩ የገበያ ትስስር ሂደቶች ላይ በቅንጅት ተናቦ መሥራት ከተቻለ አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሲኒየር ኒዩትሪሽን ስፔሺያሊስት/Senior Nutrition Specialist/ አቶ በላቸው አዱኛ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ከሚሠራባቸው በዕቅድ የተያዙ እንደ ሀዋሳ፣ ቦንጋና ሚዛን ያሉ እንሰት አምራችና ተመጋቢ አካባቢዎች የግል ካምፓኒዎች ማሽኖችን ሲያመርቱ ዩኒቨርሲቲው ቴክኒካል ሥልጠናዎች የሚሰጥ ሲሆን ከዞንና ከወረዳ ግብርና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት ማሽኖቹን በመግዛት ለተመረጡ አካላት የመስጠትና የማስተዋወቅ ሥራ በተቋማቸው ይተገበራል፡፡ አርሶ አደሩ ገቢው ሲጨምር አመጋገቡን በማስተካከል ለጤና ጠቃሚ የአመጋገብ ሥርዓት ይከተላል ያሉት አቶ በላቸው በመሆኑም የአርሶ አደሩን ገቢ መጨመር ከተልእኳችን አንዱ ነው ብለዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በቀረበው የፈጠራ ማሽን መደሰታቸውን ገልጸው የግል ካምፓኒዎች ገቢ ከመሰብሰብ ባለፈ የማኅበረሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥራው እንደ ሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባና የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት