የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምኅንድስና እና ሂሳብ (STEM) ማዕከል ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከማኅበረሰብ ጉድኝት ዋና ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ከጋሞ፣ ጎፋ፣ ቡርጂ፣ አማሮ፣ ኮንሶ፣ ባስኬቶ፣ደራሼና አሌ ዞኖች ለተወጣጡና ከ7ኛ- 12ኛ  ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች ከነሐሴ 1-30/2015 ዓ/ም ሲሰጥ የቆየው የተግባር ተኮር ሥልጠና ጳጉሜ 1/2015 ዓ/ም ተጠናቋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ሥልጠናው በመላው ሀገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን የወደፊቷን ኢትዮጵያ የሚፈጥሩና የሚሠሩ ትውልዶችን መፍጠርን ዓላማ በማድረግ የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች የተግባር ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል የተሟላ ግብዓት የሌላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ክፍተቶች የሚፈጠሩ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ተክሉ ከዚህ አንፃር ሥልጠናው ይህንን የተግባር ልምምድ ክፍተት በመሙላት ተማሪዎች ብቁ ሆነው እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ “STEM” ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር ቢንያም ወንዳለ እንደገለጹት ሥልጠናው የተማሪዎች የተግባቦትና የፈጠራ ክሂሎታቸውን ለማሳደግ የተዘጋጀና ተማሪዎች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በምኅንድስናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሥልጠናውን 155 ተማሪዎች ተከታትለው በስኬት ያጠናቀቁ መሆናቸውንም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

በአማሮ ኬሌ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ተማሪ ኢዩኤል ዮናስ በሰጠው አስተያየት ሥልጠናው በት/ቤት በጽንሰ ሃሰብ ያገኘውን ዕውቀት በተግባር የተመለከተበትና በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ያወቀበት መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዚሁ ሥልጠና ያገኘውን ግንዛቤ በመጠቀም  “SMART HOME CONTROLLER” የተሰኘ አዲስ የፈጠራ ሥራ መሥራቱን ጠቁሞ ይህም ቴክኖሎጂ ሰው በሌለበት በቤት ውስጥ የሚገኙ ኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን የመክፈትና የመዝጋት አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቅሷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት