አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ያሠለጠናቸውን 91 ወንድና 58 ሴት በድምሩ 149 የ6 ባች ተማሪዎች ለ2 ዙር  መስከረም 13/2016 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአካዳሚክ ጉዳች ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ኤባ ሚጀና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁ እና በቂ የሰው ኃይልን ማፍረት እንዲሁም የዘመኑን ዕውቀት ተጠቅሞ ቴክኖሎጂን መፍጠር፣ ማሻሻል ብሎም ማላመድ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሀገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የለውጥ ሃሳቦችን በማፍለቅና በመተግበር አርአያ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍሪያ፣ የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ እንዲሁም የባሕላዊ እሴቶች ማጎልበቻ ማዕከላት እንዲሆኑ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡  

ዶ/ር ኤባ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት ዕለቱ ለበለጠ ኃላፊነት የምትዘጋጁበትና ራሳችሁን፣ ቤተሰቦቻችሁንና ሀገራችሁን የሚጠቅም ተግባር ለመፈጸም ዝግጁ የምትሆኑበት በመሆኑ ወደ ላቀ ተግባር ለመሸጋገር ቃል በመግባት እስከ አሁን ያገኛችሁትን ዕውቀት፣ ልምድ እና ክሂሎት በተገቢ ቦታ ለመጠቀም ዝግጁ ልትሆኑ ይገባችኋል ብለዋል፡፡ ለተመራቂዎች ቀጣዩ ጊዜ ስኬት የተሞላበት እንዲሆንላቸውም ተመኝተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት ሳውላ ካምፓስ በ2015 የትምህርት ዘመን በ11 ፕሮግራሞች በቅድመ ምረቃ መደበኛና ኢ-መደበኛ መርሃ ግብሮች 2,703 እንዲሁም በድኅረ ምረቃ በአንድ ፕሮግራም 154 በአጠቃላይ 2,857 ተማሪዎችን ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ ካምፓሱ ከመማር ማስተማር ተልእኮው ባሻገር ምርምሮችን ማከናወን፣ የምርምር ውጤቶችን በታዋቂ ጆርናሎች ላይ ማሳተም፣ ምርምሮችን ወደ ፕሮጀክት ቀይሮ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግና ሌሎችም የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባራትን በማከናወን የራሱን ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ተመራቂዎች በቆይታቸው ያካበቱትን ዕውቀት፣ ክሂሎትና በአብሮነት የመኖርና የመሥራት ባህል ተጠቅመው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ፕሬዝደንቱ አደራ ብለዋል፡፡

በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ገብረመድኅን ጫሜኖ እንደተናገሩት ካምፓሱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ተማሪዎችን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሳይንስን ማስተማር ብቻ ሳይሆን በአመለካከትና በሥነ ምግባር የታነጹ፣ የሀገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ፣ ኃላፊነትን የሚቀበሉ ብቁ ተወዳዳሪዎችና ተመራማሪዎች እንዲሆኑ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተሠርቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሴቶች፣ በትምህርታቸው ደከም ላሉ እና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የተሠራ በመሆኑ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ ከካምፓሱ አጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል ተማሪ ጌታቸው ፍቅሬ ከማርኬቲንግ ማኔጅመንት ት/ክፍል 3.90 እና ተማሪ ብርሃኑ ኡማ ከጎፍኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ት/ክፍል 3.85 በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሲሆኑ ከሴት ተመራቂዎች መካከል ተማሪ መቅደስ ተስፋዬ ከሎጀስቲክስና ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት ት/ክፍል 3.86 እንዲሁም ተማሪ አሥራት ሙሉነህ ከጎፍኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ት/ክፍል 3.44 በማምጣት የዕለቱ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ 

በምረቃ መርሃ ግብሩ የሬጂስትራርና አሉምናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ የተመራቂዎችን መረጃ ያቀረቡ ሲሆን የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ተመራቂዎችን ለምረቃ አቅርበው አስመርቀዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረት ጸሐፊ ጋዜጠኛ ሳልሳዊት ባይነሳኝ ስለኅብረቱ ጥቅል መረጃ የሰጡ ሲሆን ዕጩ ዶክተር ፍስሃ በቀለ መርሃ ግብሩን መርተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት