የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት እና ከጋሞ ልማት ማኅበር ጋር በመተባበር ከከተማው ወጣት አደረጃጀት ለተወጣጡ ወጣቶች በሕይወትና የአእምሮ ውቅር    ዙሪያ ከመስከረም 8-11/2016 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕይወት ምንነት፣ የሕይወት ምርጫ፣ የአእምሮ ውቅር ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ አስተሳሰብና የአስተሳሰብ ለውጥ፣ ሰብእናና ጠባይ፣ የሰው ልጅ ራእይና ዓላማ፣ የአመራር ክሂሎት እንዲሁም የግል ሕይወትን ማሳካትና ለውጥን ማስቀጠል ለራስ፣ ለተቋሙና  ለሀገር ያለው ፋይዳ  በሥልጠናው ከተዳሰሱ  ርእሰ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ርእዮት ዓለምና ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ መብራት መንግሥቱ እንደገለጹት ሥልጠናው በሰብእና ግንባታ ዙሪያ የወጣቶችን ግንዛቤ በማሳደግ ንቁ፣ ጤናማ፣ ደስተኛ፣ አዎንታዊ አሳቢ፣ ሥራ ወዳድና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን አቅም ለመገንባት የተዘጋጀ ነው፡፡ ወጣትነት ሁሉም ነገር የሚያምርበትና ለነገ መሠረት የሚጣልበት ዕድሜ በመሆኑ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸውም ወ/ሮ መብራት ሠልጣኞችን አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ም/ኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኃ/ገብርኤል ሴኮ በበኩላቸው ሠልጣኞች አመለካከታቸውን በመቀየር ለሀገር የሚጠቅሙ መልካም ዜጎች እንዲሆኑና ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች እንዲያካፍሉ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና አሠልጣኝ አቶ መርክነህ መኩሪያ ሥልጠናው በዋናነት በሰው አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ያተኮረ ሲሆን ከቀድሞ ሕይወት ለውጥ ለማምጣትና ዓላማ መር ሕይወት ያለው፣ ሀገሩን የሚወድ፣ ስለራሱ፣ ስለቤተሰቡና ስለሀገሩ ኃላፊነት የሚሰማው ብቁ ዜጋ ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ሥልጠናው ወጣቶች በአእምሮና በስሜት ዕውቀት በልጽገው፣ በፈጠራና በምክንያታዊነት አስተሳሰባቸው ዳብሮ፣ ለሕይወት ምርጫ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት የመወሰን አቅማቸውን ከፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በግል ራሳችንን እንድናይና ክፍተቶቻችንን እንድንረዳ ትልቅ ዕድል የፈጠረልን ሲሆን በሚቀጥለው ጊዜ የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ እንድንወጣ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ ዕድሉን ያላገኙ ሌሎች ወጣቶች ሥልጠናውን የሚያገኙበት መንገድ ቢመቻች መልካም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው መጨረሻ ለሠልጣኞች የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት