በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሳውላና ጂንካ ከተሞች በሳምንት መጨረሻ መርሃ ግብር በኅብረሰተሰብ ጤና ትምህርት የ2 ዲግሪያቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች የልማታዊ የቡድን ሥልጠና ፕሮግራምን/Developmental Team Training Program /DTTP/ መሠረት በማድረግ በሳውላ ዶዛ ቀበሌ የላ ቀጠና እንዲሁም በጂንካ ብሩህ ተስፋ ንዑስ ቀበሌ በኮይዳ ቁጥር ሁለት መንደር የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር ከሰባት መቶ ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነቧቸው የጋራ መጸዳጃና ሻወር ቤት እና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መስከረም 13 እና 14/2016 ዓ/ም በይፋ ተመርቀው ለማኅበረሰቡ ተላልፈዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ፕሮጀክቶቹ የመማር ማስተማር ሥራውን ከምርምርና ማኅብረሰብ ጉድኝት ተግባራት ጋር ማስተሳሰር የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በተግባር ያሳዩ መሆኑን ተናግረው በቀጣይም መሰል ሥራዎችን ለማከናወን ማሳያ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡ የተሠሩት ፕሮጀክቶች በዘላቂነት ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ለማስቻል የአጠቃቀምና የአያያዝ ሁኔታው ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በሀገራችን ዜጎች ላይ ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል 80 ከመቶ ያህሉ ተላላፊና ከግል፣ ከአካባቢ ንጽህና፣ ከንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ችግሮች ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎቹ የማኅበረሰቡን ችግር በጥናት በመለየት የሠሯቸው ፕሮጀክቶች እነዚህን ተላላፊ በሽታዎች ከመከላከል አንፃር ጉልህ ሚና የሚጫወቱ እንዲሁም በማኅበረሰቡና በዩኒቨርሲቲው መካከል የሚኖረውን ቁርኝትና አንድነት የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው በሁለቱም ከተሞች የተገነቡት ፕሮጀክቶች የማኅበረሰቡን ተቀዳሚ ችግሮች የሚፈቱ ከመሆናቸው ባሻገር ዳይሬክቶሬቱ መማር ማስተማሩን ከማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ጋር ለማስተሳሰር ለሚያደርገው ጥረት እንደ ማሳያ የሚያገለግሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የተሠሩት ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ ተቋማት፣ ባለሀብቶች በማስተባበር የተሠሩ መሆናቸው ከማኅበረሰብ አገልግሎት ወደ ማኅበረሰብ ጉድኝት የተደረገውን የሽግግር ሥራ በተግባር ያሳየ ነውም ብለዋል፡፡ መሰል ሥራዎች በሌሎች የትምህርት መስኮችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ ዳይሬክቶሬታቸው በቀጣይ በተማሪዎች ለሚሠሩ መሰል ማኅበረሰቡን ለሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች በጀት በመያዝ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም  ቃል ገብተዋል፡፡

በኣሪ ዞን የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ አስፋው ዶሪ የጂንካ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣ በመሆኑ በከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ እንደሚታይ ተናግረው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመንደሩ ማኅበረሰቡን በማስተባበር ያስገነቡት የንጹህ  መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በተጨባጭ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የተገነባው ፕሮጀክት ማኅበረሰቡን ማስተባበር ከተቻለ መሰል ችግር ፈቺ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል ተጨባጭ ትምህርት የተወሰደበት ሲሆን ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት በጂንካ ከተማ ሕዝብና አስተዳደር ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ሽግግር ጽ/ቤት አስተባባሪ ረ/ፕ ደስታ ሀብቱ እንደገለጹት ልማታዊ የቡድን ሥልጠና ፕሮግራም/Developmental Team Training Program /DTTP/ በኮሌጁ ተግባራዊ ከሚደረጉ ማኅበረሰብ ተኮር ትምህርቶች /Community Based Education/ መካከል የ2 ዲግሪ ተማሪዎች ተግባራዊ የሚያደርጉት  ነው፡፡ በፕሮግራሙ ተማሪዎች ቀዳሚ የማኅበረሰቡን ችግሮች በመለየትና ፕሮጀክት በመቅረጽ እንዲሁም ማኅበረሰቡን በማስተባበር ችግር ፈቺ፣ የሚታይና ተጨባጭ ሥራ የሚሠሩበት የትምህርት አካልና አንዱ የመመረቂያ መስፈርት መሆኑንም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

የኮሌጁ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረ/ፕ ሙስጠፋ ግላኝ እንደገለጹት ልማታዊ የቡድን ሥልጠና ፕሮግራም በኅብረተሰብ ጤና የትምህርት ፕሮግራም ውስጥ የሥርዓተ-ትምህርት አካል ሆኖ ተግባራዊ ሲደረግ በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው ነው፡፡ በሳውላና ጂንካ ከተሞች ከተመረቁት ፕሮጀክቶች በሻገር አርባ ምንጭ በሚገኙ ተማሪዎች የተሠሩ አምስት ፕሮጀክቶች በቅርቡ ተመርቀው ለማኅበረሰቡ የሚተላለፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሳውላ ከተማ ዱዛ ቀበሌ የየላ ቀጠና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ በዛብህ እንደተናገሩት በቀጠናው በተማሪዎች የተሠራው የጋራ መጸዳጃና ሻወር ቤት ፕሮጀክት በተጨባጭ የማኅባረሰቡን ችግር የሚፈታና በተለይ ከንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል የሚረዳ ነው፡፡

በጂንካ ከተማ በብሩህ ተስፋ ንዑስ ቀበሌ በኮይዳ ቀጥር ሁለት መንደር ነዋሪ ወ/ሮ አልማዝ አስጨናቂ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የንጹህ መጠጥ ውሃ ለማግኘት ረጅም ርቀት ይጓዙ እንደነበር አስታውሰው በመንደራቸው በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አስተባባሪነት የተሠራው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቅርብ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሳውላ ከተማ ዶዛ ቀበሌ የላ ቀጠና የተገነባው የጋራ መጸዳጃና ሻወር ቤት ፕሮጀክት 261,400.00 ብር እንዲሁም በጂንካ በብሩህ ተስፋ ንዑስ ቀበሌ በኮይዳ ቁጥር ሁለት መንደር የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ 490,000.00 ብር የፈጀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ለፕሮጀክቶቹ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የዕውቅና የምሥክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት