የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል የደረጃ ዶት ኮም እህት ኩባንያ/Dereja.Com Sister Company/ ከሆነው ኢንፎማይንድ ሶሉሽንስ “Infomind Solutions” እና ከጋሞ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ጋር በመተባበር ከአርባ ምንጭ ከተማ እና ከጋሞ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ ለተመረቁ ወጣቶች በ “Dereja Academy Accelerator Program”̋ ክሂሎት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ከነሐሴ 26/2015 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ወራት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከደረጃ ዶት ኮም እህት ኩባንያ ከሆነው ከኢንፎማይንድ ሶሉሽንስ ጋር በመተባባር ላለፉት ሦስት ዓመታት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረቁ የጋሞ ዞንና አርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች ስለ“Dereja Acadamy Accelerator Program˝ ሥልጠና በመስጠት አብዘኛዎቹን ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸው በ2015 ዓ/ም ለ197 አዲስ ተመራቂ ወጣቶች በማሠልጠን ሠልጣኞቹ ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጓቸውን ተጨማሪ ክሂሎቶች እንዲኖሩዋቸው የማስቻል ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናው በበይነ-መረብ (Online)  እና በለርንንግ ማኔጅመንት ሲስተም (Learning Management System/LMS) እንደሚሰጥ የጠቆሙት አስተባባሪዋ ሥልጠናውን የወሰዱ ሠልጣኞች ካልወሰዱት ይልቅ ለሥራው ቅርበት እንደሚኖራቸውና የተሻለ የሥራ ዕድልም የሚፈጥርላቸው በመሆኑ ሠልጣኞች ሥልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ምክትል ዲንና የደረጃ አካዳሚ ዋና አሠልጣኝ መ/ር አድማሱ ጣሰው በሥልጠናው የመጀመሪያ ክፍል ሰዋዊ ክሂሎት (Soft Skill) በሚባሉ፡- የአመራርነት፣ የተግባቦት፣ ራስን የማወቅ፣ የገጽታ ግንባታ፣ ውጤታማ የሆነ ዕቅድ የማውጣት፣ የጊዜና ገንዘብ አጠቃቀም፣ ሁሉን አቀፍ ግንዛቤ የመፍጠር እንዲሁም ውጤታማነትን የመፈለግና የተቀጣሪነት ክሂሎት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን በሁለተኛው ክፍል ከሙያዊ ክሂሎች መካከል አንዱን በመምረጥ ሥልጠና እንደሚወስዱና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባለቸው ባለሙያዎችም ድጋፍና እገዛ እንደሚደረግላቸው አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡ የሥልጠናው ዋና ዓላማም አቅምን በመገንባት የተቀጣሪነት ክሂሎትን ማሳደግ እንደመሆኑ ሥልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው የምስክር ወረቀት የሚያገኙ ሠልጣኞች ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ በማድረግ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እንደሚመቻች መ/ር አዲሱ ጠቁመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት