የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ከደረጃ ዶት ኮም ድርጅት ጋር በመተባበር ለመምህራን፣ ለዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ለሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች “Key Players of Career Development Path for Fresh Graduates” በሚል ርዕስ ዙሪያ መስከረም 25/2016 ዓ/ም ሴሚናር አካሂዷል፡፡  ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዩች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ደረጃ ዶት ኮም እንደ ሀገር የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃንን ለሥራ ለማዘጋጀት እንዲሁም በሚገኘው ዕድል ሁሉ ምሩቃንን ከአሠሪዎች ጋር በማገናኘት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እና አሠሪዎች የተሻለ ዝግጅትና ብቃት ያለው ተቀጣሪ እንዲያገኙ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሥራ ፈጠራ ማዕከልም በዘርፉ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር አብዛኛው የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን ለግልና ለመንግሥት ተቋማት የሚያስፈልገውን አነስተኛ ችሎታ፡- ዕውቀት፣ ክሂሎትና አጠቃላይ ዝግጅት ያሟሉ ባለመሆናቸው በአብዛኛው የሥራ ዕድል እንደማያገኙ የገለጹት ዶ/ር ዓለማየሁ እንደተቋም ክፍተቱን በመለየትና በመሥራት ምሩቃን በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ልናበቃቸው ይገባል ብለዋል፡፡  

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ በበኩላቸው እ.ኤ.አ ከ2018 ዓ/ም ጀምሮ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ደረጃ ዶት ኮም ባደረጉት የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት የኢንተርንሽፕ ሥራዎችን እየሠሩ መቆየታቸውን ገልጸው የ2016 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ በበጀት ዓመቱ በዘርፉ ሊሠሩ የታቀዱ ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ለማከናወን አጋዥ ይሆን ዘንድ ሴሚናሩ የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

መ/ርት ስለእናት አክለውም የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከሉ ከደረጃ ዶት ኮም እና ከዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ክበብ ጋር በመተባበር በቀጣይ በዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ክበብ ለማቋቋም፣ የዲጂታል ሊትረሲ እንዲሁም የተግባቦት ክሂሎት ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱን ገልጸው ይህም ተማሪዎች በመውጫ ፈተና ወቅትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ  የሚያጋጥማቸውን የኦንላይን የመጻፍ ክሂሎት ችግር እንደሚቀርፍ ተናግረዋል፡፡

የደረጃ ዶት ኮም የትብብር ፕሮጀክቶች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደምሴ አምሳሉ እንደገለጹት ሴሚናሩ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የደረጃ ዶት ኮምን ዓላማ ተረድተው በቀጣይ ለተመራቂዎችና ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የሚሰጡ ሥልጠናዎች በተገቢው መንገድ ተደራሽ እንዲሆኑ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት ተማሪዎች የሚፈለገውን ዕውቀትና ክሂሎት ይዘው እንዲወጡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ታልሞ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙም “Role of the University Instructors for Career Development of Fresh Graduates” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የውይይት መነሻ ሠነድ ያቀረቡት የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መ/ርት ዶ/ር መቅደስ ኡርጌ ተማሪዎች በትምህርት ከሚያገኙት ዕውቀት በተጨማሪ ለሥራ ፈጣሪነትና ለተቀጣሪነት የሚያገለግሉ ክሂሎቶች ላይ ሥልጠና ቢያገኙ በሥራው ዓለም ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል፡፡ 

በሴሚናሩ “Role of The University Instructors for Career Development of Fresh Graduates” እና “Instructors’ Role as Key Players Of Career Development Path For Fresh Graduates” በሚል ርዕስ የተዘጋጁ ሁለት የውይይት መነሻ ሠነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት