በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለኮሌጁ መምህራን በኮምፒውተር የታገዘ ፈተና (Computer Based Test) አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ጥቅምት 3/2016 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ኮሌጁ ከ2016 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በወረቀት የሚሰጡ ፈተናዎችን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረትና በኮሌጁ የሚሰጡ ሁሉንም ፈተናዎች በኮምፒውተር ወደታገዘ የፈተና አስተዳደር (Computer Based Test Administration) ሥርዓት ለማሸጋገር ባስቀመጠው ዕቅድ መሠረት አሠራሩን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያግዝ ታስቦ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ ባለንበት በአሁኑ ዘመን ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ እንደመሆኑ ከ2016 ዓ/ም ጀምሮ በኮሌጁ በልዩ ሁኔታና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ ባስተቀር ፈተናዎችን በወረቀት መስጠት ሙሉ በሙሉ እንደሚቆምና በኮምፒውተር የታገዘ የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ ዶ/ር ታምሩ ተናግረዋል፡፡

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ አብነት ገ/መስቀል በኮምፒውተር የታገዘ ፈተና የፈተና አስተዳደርን በቅልጥፍና ለማከናወን፣ ፈተናዎች በእጅ ሲታረሙ ሊፈጠሩ የሚችሉ  ስህተቶችን  ለማስወገድ፣  ተማሪዎች ፈተናውን ካጠናቀቁ በኋላ ወዲያውኑ አፈፃፀማቸውን እንዲያወቁት ለማድረግ፣ በፈተና ኅትመትና ማባዛት የሚወጡ ከፍተኛ ወጪዎችን ከማስቀረት አንፃር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡ የአሠራር ሥርዓቱ ለፈተናዎች ደኅንነት ወይም ኩረጃን ከመከላከል አንጻር ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ አብነት  በአሁኑ ወቅት ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተናዎች ሳይቀሩ በዚሁ ሥርዓት የሚሰጡ በመሆናቸው ትግበራው ተማሪዎች ከአሠራሩ ጋር እንዲላመዱም ዕድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡

አቶ አብነት በኮምፒውተር የታገዘ የፈተና አሠጣጥ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የኮምፒውተር ቁጥር ውስንነት፣  የበይነመረብ ግንኙነት ችግሮች እና የኃይል መቆራረጥ ያሉ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ሂደቱን ሊያስተጓጉሉት ቢችሉም ባለው መሠረተ ልማት አሠራሩን እየተገበሩ በሂደት ማስፋፋትና ማጠናከር ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡ የኮሌጁ የተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በቀጣይም ኮሌጁ በዘርፉ ካለው የተሻለ ልምድ በመነሳት ከኮሌጁ ባሻገር ለአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች በኮምፒውተር የታገዘ የፈተና አሠጣጥ ሥርዓት ላይ መሠረታዊ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሠራም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት