የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግራንትና የትብብር ፕሮጀክቶች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ለግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን “Climate Risk Management in Agriculture” በሚል ፕሮጀክት ርዕሰ ጉዳይ ላይ መስከረም 29/2016 ዓ/ም ገለጻ ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

አሜሪካ በሚገኘው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የአየር ጠባይ ሳይንቲስት/Climate Scientist/ የሆኑት ዶ/ር ቱፋ ድንቁ በአየር ንብረት መሠረታዊ ግንዛቤ/Climate Basics/፣ በአየር ንብረት መረጃና ትንተና/Climate Data and Analytics/፣ የአየር ንብረት ተፅዕኖ በግብርና ላይ/Climate Impacts on Agriculture/፣ የአየር ንብረትን ያገናዘቡ ግብርና ተኮር ውሳኔዎች/Climate-Informed agricultural Decisions/ እና የአየር ንብረት ተፅዕኖ አስተዳደር በግብርና ልማት ላይ/Climate Risk Management in Agricultural Development/ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ማለትም ድርቅንና ጎርፍን የመሳሰሉ አደጋዎችን ሳያጋጥሙ ቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል መምህራን ተጨማሪ ዕውቀት ያዳብሩ ዘንድ በቀጣይ ለሚወስዱት ሥልጠና ቅድመ-ጥቆማ የሚሆን ገለጻ ሰጥተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የግራንትና የትብብር ፕሮጀክቶች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ በበኩላቸው የ“Climate Risk Management in Agriculture”  ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ውስጥ ካቀፋቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባለመኖሩ እንደሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ቶማስ ፕሮጀክቱ የአየር ጠባይ ለውጥን ከግብርናው ጋር ማስተሳሰር በመሆኑ ከዘርፉ ምሁራን ጋር በጋራ ለመሥራት እንዲቻል በተለይ የዩኒቨርሲቲው የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንን ማሳተፍ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተዘጋጅቶ የነበረውን የሁለት ሳምንታት ሥልጠና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች እና የተመረጡ መምህራን እንዲወስዱ ተደርጎ የተሳትፎ ምሥክር ወረቀት እንደሚሰጣቸውና ይህም በተለይ ተማሪዎች በመደበኛው የትምህርት ቆይታ ካገኙት ዕውቀት በተጨማሪ የተሻለ ለሥራ ቅጥር ብቁ፣ ተፈላጊና ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው ዶ/ር ቶማስ ጠቁመዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና የገለጻው ተሳታፊ የሆኑት ዶ/ር ደግፌ አሰፋ በበኩላቸው ሥልጠናው በሁሉም የግብርና ሳይንስ ትምህርት ፕሮግራሞች የሥርዓተ ትምህርት አካል ሆኖ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ አጭር ሥልጠና እንዲወስዱና ለዚህም የምሥክር ወረቀት እንዲሰጣቸው በማድረግ በሥራ ውድድሮች በተሻለ ሁኔታ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ይሠራል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት