የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤት የ2016 ትምህርት ዘመን የመጀመሪያ መንፈቀ ዓመት የወላጅ ጉባኤ ጥቅምት 24/2016 ዓ/ም ያካሄደ ሲሆን በ2015 የትምህርት ዘመን በ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አምስት የት/ቤቱ ተማሪዎች ስጦታ አበርክቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ መሣሪያ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የደረሰበትንና ወደፊትም ሊደርስበት የሚፈልገውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ኑሮ እድገት ደረጃ ያንፀባርቃል፡፡ ስለሆነም የትምህርት ፖሊሲው ውጤታማ እንዲሆንና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ወላጆችና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በሀገራችን የትምህርት ፍኖተ ካርታ በአዲስ መልክ ተቀርጾ ወደ ተግባር እየተገባ ባለበት ጊዜ የተማሪ ወላጆች ሚና ምን እንደሆነ ግንዛቤ እንዲያገኙ ውይይቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ ፍኖተ ካርታው በርካታ ነገሮችን የሚዳስስ በመሆኑ በዋናነት በዕውቀት የዳበረ ዜጋን ለመፍጠር ተማሪዎች ውጤታማና በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ወላጆች የበለጠ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ጉባኤው በዋናነት በትምህርት ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ሃሳብ ለመለዋወጥ ያለመ መሆኑን ገልጸው በትምህርቱ መስክ ከስኬቱ ይልቅ ጎልተው የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍና የትምህርት ጥራት ችግርን በመፍታት ሰፊና ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት ከመንግሥት ጥረት ጎን ለጎን የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና በ2015 የትምህርት ዘመን ከዐጸደ ሕፃናት እስከ 2 ደረጃ ት/ቤት በአጠቃላይ 1,697 ተማሪዎች ተይዘው የመማር ማስተማር ሥራው ሲከናወነ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ የ12 ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ውጤትን በተመለከተ 20 በመቶ ተማሪዎች ከማለፊያ ነጥብ ወይም 50% በላይ እና 80 በመቶ ተማሪዎች ከ50% በታች እንዲሁም አምስት ተማሪዎች ከ500 በላይ ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

በ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና 566 ነጥብ ያመጣው ተሸላሚ ተማሪ አስታውስ አምሳሉ የመምህራኑና ወላጆቹ እገዛ ላይ የራሱ ጥረት ታክሎበት ውጤቱን ማምጣት መቻሉን ተናግሯል፡፡ ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ በራሱ የአጠናን ዘዴ እንደሚያጠና የገለጸው ተማሪ አስታውስ የመርጃ መጻሕፍትን በመዋስ፣ መምህራንን በልዩ ትኩረት በመከታተልና አዳዲስ ሃሳቦችን በልዩነት ጽፎ በመያዝ ትምህርቱን በትኩረት እንደሚከታተል ገልጿል፡፡

በውይይቱ ‹‹የወላጆች ሚና በልጆች ትምህርትና ባህርይ›› በሚል ርእስ በመምህር ፈቃዱ መኩሪያ አጭር ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን የዩኒቨርሲቲውና የት/ቤቱ አመራሮች፣ የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢና አባላት እና መምህራን ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት