አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2015 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አንድ ኮሌጅ፣ ዘጠኝ ት/ክፍሎች/ፋከልቲዎች፣ ሁለት ተመራማሪዎች እና ሦስት የአስተዳደር ሠራተኞች ዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ጥቅምት 27/2016 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በተቋማት አስተዳደራዊ አሠራር ውስጥ የተለየ ሥራ በመሥራት የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሠራተኞችን መሸለምና ዕውቅና መስጠት እንዲሁም አነስተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሠራተኞችን ገምግሞ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የተለመደ አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በበጀት ዓመቱ ዩኒቨርሲቲው ተልእኮዎችን መነሻ በማድረግ በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በአስተዳደርና ልማት ዘርፍ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ኮሌጆች፣ ት/ክፍሎች፣ ፋከልቲዎችና ግለሰቦች ዕውቅና የሰጠ መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው ገልጸዋል፡፡

የዕውቅናና ማበረታቻው ዓላማ በዋናነት ሽልማት የተሰጣቸውን ግለሰቦች፣ የትምህርት ክፍሎችና ኮሌጆች ለላቀ ሥራ ይበልጥ ማነሳሳትና በቆይታቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና መስጠት እንዲሁም ሌሎች የዩኒቨርሲቲውን መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ሠራተኞች ለላቀ ሥራ ማነሳሳት ሲሆን መሰል የዕውቅናና የሽልማት ፕሮግራሞች በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ዘርፎች የሚሠሩ ሥራዎችን ከማነቃቃትና ውጤታማነቱን ከማሻሻል አንጻር የሚኖራቸው ፋይዳ ጉልህ በመሆኑ በቀጣይ በየዓመቱ ለማካሄድ እንደሚሠራ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ የሽልማቱ ዋነኛ መስፈርቶች የተለየና አዲስ ሥራ መሥራት እንዲሁም በተሠማሩበት የሥራ መስከ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ መቻል ሲሆን በመማር ማስተማር ዘርፍ በ2015 ዓ/ም የመጀመሪያ ዲግሪ መውጫ ፈተና መቶ በመቶ ተማሪዎችን ማሳለፍ የቻሉ ሰባት የትምህርት ክፍሎች፣ ሁለት ፋከልቲዎችና አንድ ምርጥ ኮሌጅ ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ 

በዚህም መሠረት ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ለ‹‹Rural Development and Agricultural Extension››፣ ለ‹‹Natural Resources Management›› እና ለ‹‹Horticulture››፣  ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ  ለ‹‹Biology›› እና  ለ‹‹Chemistry››፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ለ‹‹Hotel and Tourism Management››፣ ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ‹‹Pharmacy›› ትምህርት ክፍሎች እንዲሁም ከውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለ‹‹Hydraulic and Water Resources Engineering›› እና ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለ‹‹Civil Engineering›› ፋከልቲዎች ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቷል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በመውጫ ፈተና በሦስት ት/ክፍሎች በሚገኙ አራት ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ በማሳለፉና በዚህም ከሌሎች ኮሌጆች የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገቡ የዓመቱ ምርጥ ኮሌጅ ዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡

በተመሳሳይም በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ከታተሙት የምርምር ሥራዎች ቁጥርና ብዛት ባሻገር የምርምር ሥራው የታተመበት ጆርናል ደረጃና ታዋቂነት፣ በምርምር ሥራው ላይ የተመራማሪው ሚና፣ የምርምር ሥራው ለዩኒቨርሲቲው ካለው ቅርበትና ከሌሎች መመዘኛዎች አንጻር ታይቶ በዓመቱ 8 የምርምር ሥራዎችን በታዋቂ የምርምር ጆርናሎች ላይ ማሳተም የቻሉት ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ የዓመቱ ምርጥ አሳታሚ/Best Publisher of the Year/ በሚል ከባዮሎጂ ት/ክፍል ዕውቅናና ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ከተለያዩ አጋር አካላት ፈንድ በማፈላለግ የትብብር ፕሮጀክቶችን በማምጣት በዓመቱ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ግራንት ማስገኘት የቻሉት በባዮሎጂ ት/ክፍል የባዮቴክኖሎጂ ተመራማሪና መምህር የሆኑት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ የዓመቱ ምርጥ የትብብር ፕሮጀክቶች አሸናፊ/Best Collaborative Project Grant Winner of the Year/ በመባል ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ከአስተዳደር ዘርፍ የጸጥታና ደኅንነት ጽ/ቤት ኃላፊ ባሻ አበራ ወርቁ በበጀት ዓመቱ ለአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሠላማዊና ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ከመፍጠር አንጻር ለተጫወቱት ከፍተኛ ሚና ዕውቅናና ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን የጠቅላላ አገልግሎት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ወልዴ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ውስጥ በሠሩት የገቢ ማስገኛ የግብርና ልማት ሥራ በተመሳሳይ መልኩ ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በተጨማሪም በጸጥታና ደኅንነት ዘርፍ የጥበቃ ሠራተኛ የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ እንደሻው በበጀት ዓመቱ አስፈላጊ ፍተሻ በማካሄድ ለዩኒቨርሲቲው ንብረት ጥበቃና ደኅንነት ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦና ላሳዩት ትጋት ዕውቅናና ሽልማት አግኝተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ካሉ ኮሌጆች፣ ት/ቤቶችና ኢንስቲትዩቶች በመውጫ ፈተና በአራት ፕሮግራሞች በማሳለፍ የላቀ አፈፃፀም ተሸላሚ የሆነው የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ በሰጡት አስተያየት የተገኘው ዕውቅና የትምህርት ክፍሎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዕውቅናና ሽልማቱ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያነሳሳ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ደግፌ በቀጣይ በሁሉም መስክ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዘገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትጋት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

የዓመቱ የትብብር ፕሮጀክቶች አሸናፊ/Best Collaborative Project Grant Winner of the Year/ በመባል ዕውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው የባዮቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ከዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸው ዕውቅናና ሽልማት በእጅጉ እንዳስደሰታቸውና ተቋሙ ካሉት በርካታ ልምድ ያካበቱ ተመራማሪዎች አንጻር ሽልማቱን አገኛለሁ ብለው እንዳልጠበቁ ተናግረዋል፡፡ የተሰጣቸው ዕውቅናና ሽልማት ለቀጣይ ሥራዎች እንደሚያነሳሳና የሞራል ስንቅ እንደሚሆን የገለጹት ዶ/ር አዲሱ ከዚህ ቀደም ከተሠሩ ፕሮጀክቶች በገንዘብ መጠን፣ ጥራትና ተደራሽነት የተሻሉ ፕሮጀክቶች በቅርቡ ይፋ ሆነው ሥራ የሚጀምሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ትስስርና ግንኙነት መፍጠር፣ የሥራ ውጤትንና ራስን ሳይሰለቹ ማስተዋወቅ፣ የውድድር ፕሮፖዛሎችን በጥንቃቄና በጥራት ማዘጋጀትና በፕሮፖዛል ዝግጅት ጊዜ የሌላ ትምህርት መስክ ምሁራንን ማሳታፍ ግራንቶችን የማሸነፍ ዕድልን የሚያሰፉ መሆናቸውንም ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል፡፡

በዕውቅናና የሽልማት ፕሮግራሙ ለት/ክፍሎችና ፋከልቲዎች እንዲሁም ለዓመቱ ምርጥ ኮሌጅ የላፕቶፕ ኮምፒውተሮችና የምሥክር ወረቀት፣ ለተመራማሪዎች ዘመናዊ ታብሌትና የምሥክር ወረቀት እንዲሁም ለአስተዳደር ሠራተኞች የዘመናዊ ስልክና የአልባሳት የማበረታቻ ሽልማት እና የምሥክር ወረቀት ተበርክቷል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት