አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በኦንጎታ ማኅበረሰብና ቋንቋ ላይ እያካሄደ ያለው ጥናት የደረሰበት ደረጃ ሪፖርት ለሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ጥቅምት 24/2016 ዓ/ም ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት በኦንጎታ ማኅበረሰብና ቋንቋ ላይ እየተካሄደ ያለው ጥናት በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ምሁራንን ለአንድ ሀገራዊ ሥራ ያስተሳሰረ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው ሥራው በሌሎችም መስኮችም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኩሴ ጉዲሼ በበኩላቸው የኦንጎታ ማኅበረሰብ  በደቡብ ኦሞ ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን ቁጥራቸው በጣም እየተመናመነ ለመጥፋት የደረሰ ማኅበረሰብ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ይህንን በማረዳት የማኅበረሰቡን ባህል፣ ታሪክ፣ ማንነት ሰንዶ ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅና ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እየሠራ ያለው ሥራ የሚያበረታታ እንደሆነም ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ ጂንካና አካባቢው መሰል የምርምርና ጥናት ሥራዎችን ለማከናወን ምቹ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ኩሴ በቀጣይ ጊዜያትም በመስኩ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የኦንጎታ ቋንቋ በዩኒቨርሲቲው ግራንት የምርምር ፕሮጀክት ሆኖ ሥራው ከተጀመረ በኋላ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ካለው ቅርበት አንፃር በትብብር መሥራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ከሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር በሥራው ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ እንደሚሠራ ም/ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡ የኦንጎታ ማኅበረሰብን ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ዕውቀትና ፍልስፍና በተለያዩ መንገዶች ሰንዶ ማስቀመጥ መቻልና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ለሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ ስኬት መሆኑንም ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

የኦንጎታ ቋንቋ ምርምር ፕሮጀክት ቡድን መሪና ተመራማሪ ዶ/ር ስንታየሁ ሰሙ በጥናቱ ላይ ከሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ሰባት አባላት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ዶ/ር ስንታየሁ በዕለቱ “Gender, Number, Subject Pronouns and Time Adverbs of Ongota” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በጥናቱ ቋንቋው ስም፣ ፆታ፣ ቁጥር፣ የጊዜ ተውሳከ ግሥ፣ የስምና ተውላጠ ስም አሰያየም፣ በሳምንቱ ውስጥ ያሉ ዕለታት ስያሜ እንዲሁም የግሥና የዓረፍተ ነገር አወቃቀርን የተመለከቱ መረጃዎች እየተሰባሰቡ እንዲሁም እየተሰነዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር፣ የኦንጎታ ማኅበረሰብ ቋንቋ ጥናት ቡድን አባልና ተመራማሪ ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሌ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን “Indigenous Medicinal knowledge and Heading Practice of the Ongota” በሚል ርዕስ እያከናወኑ ሲሆን በጥናታቸው የኦንጎታ ማኅበረሰብ 41 የሰው በሽታ፣ ስምንት የእንስሳት በሽታ፣ ሰባት የሰውነት ክፍሎችን በማሸት የነርቭ ሕክምና እንዲሁም የባህላዊ እምነት ከበራ ሥርዓቶችን በመፈጸም ከሰባት በላይ የበሽታ ዓይነቶችን የመፈወስ ዕውቀት እንዳለው በጥናቱ መረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ጥናቱ በማኅበረሰቡ  ለመድኃኒትነት 34 ዕፅዋቶችን፣ አምስት ማዕድናትን እንዲሁም ስምንት የእንስሳት ተዋጽኦዎችን እንደሚጠቀም መለየቱንም ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት