አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ከጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ለክልሉ ባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት “ቅርሶቻችን ለዘላቂ ልማትና ሀገራዊ ፋይዳ” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ በኢንታጀብልና ኢትኖግራፊ፣ በአርኪዮሎጂ፣ በፓሊዮንቶሎጂና ፓሊዮአንትሮፖሎጂ እንዲሁም ፊሎሎጂ ታሪክና ሥነ-ጽሑፍ ቅርሶች ጥበቃ፣ እንክብካቤና ልማት ዙሪያ ከኅዳር 11-12/2016 ዓ/ም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ውብና ማራኪ የሆኑ ቅርሶችና ባህሎች ባለቤት እንደመሆኗ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች የሚገኙበትና የልዩ ልዩ ባህላዊ ቅርሶችና ቋንቋዎች ባለቤት ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት የባህልና ቋንቋ ምርምር ኢንስቲትዩት በማቋቋም ለሀገር ሠላምና አንድነት በእጅጉ ጠቃሚ የሆኑትን የጋሞ ዱቡሻ፣ የደራሼ ፊላ እና ሌሎች የደቡብ ክልልና የሀገራችን ባህላዊ ሀገር በቀል እሴቶችን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥልጣናውም የክልሉን ባህላዊ ቅርሶች ለመንከባከብ፣ ለማሳደግና በተሻለ ደረጃ ለሀገራዊ ሠላምና ዕድገት ለመጠቀም እንዲቻል ሊሠሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ያለንን ግንዛቤ ለማዳበር መዘጋጀቱን ፕሬዝደንቱ አክለዋል፡፡  

የጋሞ ዞን ም/አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ልሳነወርቅ ካሳዬ ቅርሶች ከምን ጊዜውም በተለየ ፍጥነት በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እንዲሁም ሉላዊነት ምክንያት ለአደጋ እየተጋለጡና እየጠፉ እንደሚገኙ ገልጸው ይህንንም መሠረት በማድረግ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ቅርሶቻችንንና ባህሎቻችንን በአግባቡ በመመዝገብ፣ በማጥናት፣ በመጠበቅ፣ በማጎልበትና ለቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ እንዲሁም ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ልሳነወርቅ አክለውም የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች በተጨማሪ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ ዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ እንዲሁም የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የማኅበረሰብ ንቅናቄ መድረኮች በማዘጋጀትና በመሥራት የዱቡሻ ወጋን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ኃይሉ ቅርስ የሁሉም ሰው ጉዳይ በመሆኑ ለማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን ከተመዘገበ በኋላ ያለውን አደጋ ለመከላከል በተቀናጀና በዕውቀት ላይ በተመሠረተ መንገድ ልንጠብቀው እንዲሁም በተዋረድ የድርሻችንን ወስደን ልንሠራበት እንደሚገባ መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የኢንታንጀብል ቅርስ ተመራማሪ  ወ/ሮ ቀለሟ መኮንን እንደገለጹት የሥልጠናው ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከክልሎች ጋር በመሆን ከቅርሶች ጥበቃ ልማትና ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ የጀመረውን ቅንጅታዊ አሠራር በየመስኩ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ በማይዳሰሱ ቅርሶች፣ በአርኪዮሎጂ፣በፓሊዮንቶሎጂ ቅርሶች፣ በታሪክና ሥነ ጥበብ ዘርፍ ጽንሰ ሃሳብና ተግባርን ባሳለጠ መልኩ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የሙዚየም ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው ታሪክ የአንድን ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ክንውኖች እንደሚያስረዳው ሁሉ ቅርሶች ደግሞ በትክክለኛ መንገድ የአንድን ማኅበረሰብ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች ያሳያሉ ብለዋል፡፡ ታሪክ በታሪክ ምሁራን እንደሚጻፍ፣ እንደሚሠነድ፣ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ በቅርሶች ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ፣ መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ በሙዚየሞች አሰባስቦ ለዓውደ ርዕይ ማዋል፣ ለትምህርት፣ ለጥናትና ምርምር ማዋልና መዝግቦ መያዝ እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡ ታሪክ የሌለውና ቅርሱን በአግባቡ ያልተረዳ ሕዝብ በጣም አስቸጋሪ ለሆኑ ትርክቶች ተጋላጭ ስለሚሆን ታሪክ የመጠበቅ የመንከባከብ ጉዳይ ቅርስን ከመጠበቅና ከመንከባከብ ጉዳይ ተለይቶ ሊታይ እንደማይችል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የባህላዊ ቅርሶች ምንነትና ሊደረጉ የሚገቡ እንክብካቤዎችን አስመልክቶ የመወያያ ሠነድ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ በቅርሶች ዘለቄታዊ ጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ ግድየለሽነት፣ ወራሪ ባህሎች፣ የቱሪዝም ተጽዕኖ፣ ሕገ ወጥ የቅርስ ዝውውርና ዘረፋ፣ ጦርነት እንዲሁም የኢንደስትሪና የከተሞች መስፋፋት እና ለመካነ ቅርሶች ትኩረት አለመስጠት የተጋረጡ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ሲሆኑ ይህንንም ለመከላከል ለቅርሶች እንክብካቤና ጥበቃ የማድረግ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን የመስጠት፣ ሙዚየሞችን የማደራጀት፣ ቅርሶችን የመመዝገብ እና መጤ ባህሎችን የመከላከል ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በምርምር የዱቡሻ ወጋንና ፊላን  በዩኔስኮ/UNESCO/ ለማስመዝገብ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ቋንቋዎችንም ከመጥፋታቸው በፊት የመሠነድና ቋንቋው የሚያንሠራራበትን ሁኔታ እያመቻቸ መሆኑን ገልጸው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሥልጠና የመስጠት፣ ሙዚየም የመገንባትና የማደራጀት ሥራዎች በሂደት ላይ መሆናቸውን ዶ/ር ሰኢድ ተናግረዋል፡፡  

ቅርስን ማስመዝገብ ብቻውን ውጤት ሳይሆን ቅርሱን በዘላቂነት ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር መሥራት ያስፈልጋል ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናት፣ ጥበቃና ልማት ቡድን መሪ አቶ ሙሉነህ ተፈራ ምንም እንኳን ቅርሶች ላይ ያሉ ፈተናዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ቢመጡም የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቅርሶችን የመመዝገብ፣ የማጥናት፣ ከቱሪዝም አንጻር በማስተዋወቅ ማኅበረሰቡ ቅርሱን እንዲጠብቅ በማስተማር የበለጠ እንዲጎለብትና ማኅበረሰቡም እንዲጠቀም ብሎም ከትውልድ ወደ ትውልድ የታሪክ አሻራቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ እየተሠራ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቡድን መሪው አክለውም በሀገር ደረጃ 11 ዓለም አቀፍ መካነ ቅርሶች በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገባቸውንና ኢትዮጵያም በአፍሪካ ቅርሶችን በማስመዝገብ ረገድ 1ኛ መሆኗን  ተናግረዋል፡፡

የዱቡሻ ወጋና የደራሼ ፊላ  ቅርሶች ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በሚል የመወያያ ሠነድ ያቀረቡት የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ታሪክ ቅርስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንድይፍራው ከተማ ሲሆኑ ከተለያዩ የጥናት ውጤቶች ለማየት እንደተሞከረው የዱቡሻ ሥርዓት ትልቅ ጥበቃና እንክብካቤ የሚፈልግበት ወቅት ላይ እንዳለና የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች እየደረሱበት መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም እነዚህን ተጽዕኖዎች መፍታት የሚቻለው የተለያዩ ጥናቶችንና ሥልጠናዎችን በማካሄድ እሴቱ በዘላቂነት ጥበቃና እንክብካቤ ተደርጎለት እንዲጠበቅ ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል፡፡ ሥርዓቱም ካለው ማኅበራዊ ፋይዳ አንጻር ለሠላም ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ወጣቶች ላይም መሥራት እንደሚገባ አቶ ወንድይፍራው ገልጸዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው ችግሮችን እንዴት መከላከል እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ገልጸው በቀጣይ በጋራ በመሥራት ቅርሶችን ልንጠብቃቸውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ልናሻግራቸው ይገባል ብለዋል፡፡ በሥልጠናውም ከፌዴራል ቅርስ ጥበቃ፣ ከክልሉ ከተለያዩ ዞኖች የመጡ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎችና የዞን ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን ዘጠኝ ምርምርን መሠረት ያደረጉ ሠነዶች ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት