አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ ላይ ሱፐርቫይዘሮች በሚሰጧቸው አስተያየቶች ላይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠቃቀማቸውን ለማሻሻል የሚያስችል ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ኅዳር 15/2016 ዓ/ም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ የምርምር ሥራ ዋና ዓላማው ለተለያዩ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት መሆኑን ገልጸው ምርምር ሁል ጊዜም ጥራት ያለው፣ ሊተገበር የሚችልና አዲስ ዕውቀት ሊፈልቅበት ይገባል ብለዋል፡፡ የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ከምሥረታው ጀምሮ የተለያዩ መደበኛና ግራንድ ምርምሮችን እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዲኑ በዕለቱ ይፋ የተደረገው የምርምር ፕሮጀክትም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመለየት እንዲሁም በዘርፉ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎችን ከማሻሻል አንጻር የጎላ ሚና እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡

የባህልና ቋንቋ ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ በቋንቋና ባህል ብዝሃነት ላይ በማተኮር የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን አሁን ላይ በኢንስቲትዩቱ 48 መደበኛና አዲሱን ፕሮጀክት ጨምሮ ሦስት ግራንድ የምርምር ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በዕለቱ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት የትምህርት ጥራት ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ይህንን እንደ ጅማሬ በመውሰድ በቀጣይ መሰል ግራንድ የምርምር ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህርና  የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ  ዶ/ር አባተ ደምሴ የፕሮጀክቱን ዓላማ ለማስተዋወቅ መርሃ ግብሩ መሠናዳቱን ገልጸው ጥናቱ ሱፐርቫይዘሮች ለተማሪዎቻቸው የሚሰጡት አስተያየት የሚፈጥረውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ መለየት በዋናነት የቋንቋ አጠቃቀማቸውን ለመዳሰስ የሚሠራ ነው፡፡ እንደ ተመራማሪው ገለጻ ለተማሪዎች የሚሰጡት ግብረ መልሶች የቋንቋ አጠቃቀም ስሜትንና ሞራላቸውን የሚነካ ከሆነ ስሜታቸው ተጎድቶ ተስፋ ሊያስቆርጣቸውና ወደ ኋላ ሊዘገዩ ስለሚችሉ ሱፐርቫይዘሮች ግብረ መልስ ሲሰጡ የሚጠቀሙበት ቋንቋ ምን እንደሚመስል መዳሰስና ከኋላም ግንዛቤ መፍጠር የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት ነው፡፡

የጥናት ፕሮጀክቱ ተማሪዎች በሰዓት ሥራቸውን አጠቃለው በወቅቱ እንዲመረቁ ለማስቻል ብሎም የመመረቂያ ጽሑፎችን ጥራትና ብቃት ደረጃ ከፍ ከማድረግ አንጻር የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ዶ/ር አባተ አመላክተዋል፡፡ የጥናቱ በጀት በዩኒቨርሲቲው እንደሚሸፈን የገለጹት የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ፕሮጀክቱ አንድ ሚሊየን ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በጀት የተመደበለት መሆኑንና በአራት ዓመት ቆይታ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ አባል ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በመዝጊያ ንግግራቸው መድረኩ የተሳካ የውይይት ቆይታና ለሥራው ጥሩ ግብዓት የተገኘበት እንደነበር ጠቅሰው በጋራ መሥራት ከተቻለ በርካታ ችግሮችን መሻገር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት የጥናቱን ሂደት ለማሳለጥ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው ለሀገር ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ በሂደቱ የሚያጋጥሙ ተጋዳሮቶችን ተቋቁሞ በሙሉ ኃላፊነት በትብብር በመሥራት የተሟላ መረጃ የሚገኝበትን ሂደት ለመፍጠር እንተጋለን ብለዋል፡፡

የምርምር ሥራው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በዋቸሞ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወን ይሆናል፡፡

በመርሃ ግብሩ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነሰብ ኮሌጅ ዲን፣ የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር፣ የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር፣ ለጥናቱ ከተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል ተጠሪዎችና የድኅረ ምረቃ አስተባባሪዎች፣ የፕሮጀክቱ ተመራማሪዎችና በጥናቱ የሚሳተፉ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት