የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የብዝሃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ከዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ጽ/ቤት እና ከምርምር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ኅዳር 20/2016 ዓ/ም በዶርዜ ሆሎኦና ላካ ቀበሌ በሚገኘው የዩኒቨርሲቲው የብዝሃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል እንዲሁም በአርሶ አደር ማሳ ላይ የሚገኙ የቢራ ገብስ ዝርያዎች የመስክ ምልከታና የዝርያ መረጣ አካሂዷል፡፡  ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ከበደ ጆቢር እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው እንሰትን ጨምሮ በርካታ ምርምሮችን በማካሄድ ግኝቶቹን በተግባር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከተ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የብዝሃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ተመራማሪዎችም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የቢራ ብቅል ገብስ ምርጥ ዝርያዎችን ከተለያዩ ቦታዎች አምጥተው በማጥናትና በማሻሻል ውጤታማ የሆነውን ለይተው ለአርሶ አደሩ ለማድረስ በትጋት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ከበደ አክለውም አርሶ አደሮቹ በመስክ ምልከታው ሂደት ውጤታማ የሆነውን የቢራ ብቅል ገብስ በመለየትና ወደ ማሳው ወስዶ በማባዛት ምርታማነቱን ካላቸው ዕውቀት ጋር አቀናጅተው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከጎናቸው በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ዶ/ር ከበደ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የብዝሃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሽቴ ጋተው የመስክ ምልከታው ዓላማ በጥናት ከተመረጡት 10 የገብስ ዝርያዎች መካከል አርሶ አደሩ በምርታማነት የተሻለውን ለይቶ እንዲመርጥና በቀጣይ ወደ ራሱ ማሳ በመውሰድ ያገኘውን ልምድ መነሻ በማድረግና የራሱን ተሞክሮ በማከል የተሻለ ገቢ እንዲያገኝና ኑሮውን እንዲያሻሽል ብሎም ልምዱን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲችል ማብቃት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ በበኩላቸው በአርሲና በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ተዘርተው ጥሩ ውጤት ያመጡ የተለያዩ ዝርያዎችን ከአርሲ ቁልምሳ የግብርና ምርምር ማዕከል በማምጣት እንዲሁም ምርታማ የሆኑ ዝርያዎችንም ከጋሞ ደጋማ አካባቢዎች በመውሰድ ለሙከራ በተዘጋጁ ትንንሽ 40 ማሳዎች ላይ መዘራታቸውን ገልጸው እነዚህ ዝርያዎች በዶርዜ አካባቢ ካሉት ዝርያዎች የተሻለ ምርት ማስገኘታቸውን፣ በሸታን ከመቋቋም፣ ከግሽበት አንጻር አርሶ አደሩ አይቶ በመምረጥ፣ በቀጣይ ወደ ማሳው ወስዶ በመዝራት የተሻለ የቢራ ገብስ አቅራቢ እንዲሆንና ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው ለሌሎች እንዲተርፉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የብዝሃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ተመስገን ዲንጋሞ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚመረተው የቢራ ገብስ ምርት ካለው ሀገራዊ ፍጆታ አንጻር በቂ ባለመሆኑ በምርምር የተደገፉና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ የገብስ ዝርያዎችን ወደ ማኅበረሰቡ በማምጣትና ያለውን እምቅ ኃይል ተጠቅሞ ምርቱን በማሳደግ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ታስቦ የተካሄደ ጥናት መሆኑን ገልጸዋል፡፡  በመስኩ ላይም የተሻለውን ዝርያ በመምረጥ በቀጣይ ወደ ማኅበረሰቡ ወስዶ ሙከራ በማድረግ ዝርያዎቹን የማስፋፋት ሥራ እንደሚሠራና አርሶ አደሩም ትልቁን ሚና የሚጫወት ሲሆን ዩኒቨርሲቲውም ከማኅበረሰቡ ጎን በመሆን መደገፉን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ተመራማሪው አክለውም ለቢራ ብቅል ግብዓት የሚሆኑ የገብስ ዝርያዎችን በበቂ ሁኔታ በማምረት ረገድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ 1 እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ 11 ላይ የምትገኝ ሲሆን አብዛኛው የገብስ ምርት የሚመረተው በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ ተወካይ አቶ ጌታሁን መዓዛ እንደተናገሩት አርሶ አደሩ የተመረጠውን ዝርያ ወስዶ በራሱ ማሳ ላይ ተግባራዊ እንዲያደርግና ትርፋማ እንዲሆን የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች በትኩረት ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉላቸው በማድረግ ውጤታማ የሆነ ሥራ እንዲሠራ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ከእንሰት ጀምሮ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ አርሶ አደሩን የሚለውጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እያበረከተ ላለው ትልቅ አስተዋጽዖ ምሥጋናቸውን ችረዋል፡፡ በቀጣይም ከግብርና ቢሮዎች ጋር በቅንጅት በመሥራት አርሶ አደሩን ይደግፍ ዘንድ አቶ ጌታሁን ጠይቀዋል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው በተለያየ መንገድ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አዳዲስ ግኝቶችን በማምጣት በርካታ ድጋፎች እያደረገ በመሆኑ አመስግነው  የመጣውን ምርጥ የገብስ ዝርያ ወስደው በአካባቢያቸው ለመተግበር ይችሉ ዘንድ የዩኒቨርሲቲው፣ የአካባቢው የግብርና ባለሙያዎችና የወረዳው አመራሮች ክትትልና ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት