በዩኒቨርሲቲው የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በዓለም አቀፍ ደረጃ 20ውና በኢትዮጵያ 19ው የፀረ ሙስና ንቅናቄ ቀን ‹‹ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፤ በኅብረት እንታገል›› በሚል መሪ ቃል ኅዳር 25/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ሙስናና ብልሹ አሠራር ከባድና ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን ጠቅሰው የንቅናቄው ዓላማ በሙስና መከላከያ መንገዶች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ሀብት ተመድቦ ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥባቸውና ሰፊ ማኅበረሰብ የሚገኝባቸው የሕዝብ ተቋማት በመሆናቸው በዩኒቨርሲቲዎች ሥራ አፈጻጸም ብልሹ አሠራርና ሙስናን ማስቀረት ለሀገር እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ሀብትና የሥራ ሰዓትን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም ሥራዎችን መመሪያና ደንብን ተከትሎ ማከናወን ከሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንደሚጠበቅ የገለጹት ፕሬዝደንቱ በተለይም በአመራርነት ላይ የምንገኝ ሰዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ሙስናን በመታገል ረገድ የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ  መሆኑን በመገንዘብ በተቋሙ ባሉ ካምፓሶች በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮችና የዘርፉ ሥራ አስፈጻሚ አካላት ጋር የሥነ ምግባር ጥሰት፣ የአሠራር ሥርዓት፣ የሥነ ምግባር ብልሹነት ምንጮች እና የመፍትሔ ሃሳቦች ዙሪያ ከኅዳር 11-17/2016 ዓ/ም ‹‹የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ማኅበረሰብ የፀረ ሙስና ንቅናቄ ሳምንት›› ሆኖ የሥነ ምግባር ግንባታ ግንዛቤ ማጎልበቻ የጋራ ውይይት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ሙስናን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ዓለም አቀፍ ጥረትና ተነሳሸነት በመደገፍ ተቋሙ የሥነ ምግባር ግንባታና የሙስና መከላከል ላይ በቁርጠኝነት መሥራት፣ በተደራጁ የሥና ምግባር ክፍሎች ብልሹ አሠራሮችን በመጠቆም ተጣርተው ለሚመጡ ጥቆማዎች በየደረጀው መረጃን መሠረት ያደረገ አስተማሪ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲሁም የሕግና ፍትሕ አካላት ክስ በመመሥረት ወንጀለኞችን በተገቢው መልኩ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግና እየተሸረሸረ ያለውን የሕዝብ አመኔታ እንደገና ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠሩ ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የውይይት መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋ ት/ክፍል መምህር  ዶ/ር ያሲን ሁሴን በሙስና ምንነት፣ ሙስና በዓለም አቀፍ፣ በአፍሪካና በሀገራችን ደረጃ ያስከተለው ጉዳት፣ ሀገራዊ የሙስና መከላከያ መንገዶች፣ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችና የመሳሰሉትን ዳስሰዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት አስተዳዳርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ 20ው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ንቅናቄ በዩኒቨርሲቲው በዚህ መልኩ መከበሩ መልካም መሆኑን ተናግረው ሙስናን ለመዋጋት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በጋራ መቆም እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በንቅናቄው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን በተማሪዎች ጭውውት፣ ጥያቄና መልስ ውድድርና ፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በጥያቄና መልስ ውድድሩ ከ1-4 ለወጡ ተማሪዎች የሞባይል ካርድ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡ 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት