በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 18ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ‹‹ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ኅዳር 24/2016 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዓሉን ስናከብርም ሆነ ካከበርን በኋላ ጎልቶ ሊታይ የሚገባው የኢትዮጵያ አንድነትና እኩልነት መሆኑን ገልጸው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንነታቸው በመኩራት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ እሴቶቻቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ አክለውም በመከባበር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠርና በኢኮኖሚ የበለፀገች ሀገር ለመሆን የተሻለ መንገድ የተዘረጋበትና ሕገ መንግሥት የፀደቀበት ወቅት በመሆኑ አካባቢን በማልማት እና ከመንግሥት ጋር በመሥራት ሕዝቦች ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንዲሁም እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ታሪኮቻችንን በሚያኮራ መልኩ ለማስቀጠል በጋራ  መኖር፣ መሥራት፣ መማርና መመራመር እንዲሁም የሚመጥን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደገለጹት እንደ ዩኒቨርሲቲ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ ስብጥር የሆነ አንድነትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡ የዜጎች መብት ተከብሮ እንዲኖርና ሰላም እንዲረጋገጥ ለማኅበረሰቡ የተለያዩ ግንዛቤዎችን ማስጨበጥ ተገቢ መሆኑን ገልጸው ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእንኳን አደረሰን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ በበኩላቸው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሲከበር የመጣውን ትሩፋት በመንከባከብ እና በመጠበቅ ቀጣይነት እንዲኖረው እንዲሁም ማኅበረሰቡ የትሩፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ማገናኘትና ማስተዋወቅን ዓላማው ያደረገው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች በመደጋገፍ፣ በመቻቻል ለሀገራቸው እድገት እንዲቆሙ የሚረዳ እንደሆነና “ኢትዮጵያ የኔ እኔም የኢትዮጵያ ነኝ” በሚል ስሜት መሥራት ከተቻለ ትልቅ ትሩፋት ሊያመጣ እንደሚችል የታየበት ክብረ በዓል መሆኑን ዲኑ አክለዋል፡፡

በዕለቱ የውይይት መነሻ ሠነድ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የሥነዜጋና የሥነምግባር ትምህርት መምህር ዶ/ር ያሲን ሁሴን በኅብረብሔራዊ ፌዴራሊዝምና የሰላም ግንባታ፣ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ምንነት፣ የፌዴራሊዝም ጥቅሞችና ተግዳሮቶች፣ ኅብረብሔራዊ ፌዴራሊዝምን ከመተግበር አንፃርና ስለፌዴራሊዝም ያለን አናሳ አመለካከት ዙሪያ ገለጻ አቅርበዋል፡፡ ኅብረብሄራዊ ፌዴራሊዝም ማለት ብዝኃነትን መሠረት አድርጎ  በአንድ ሀገር ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶችን መተግበር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ዶ/ር ያሲን አክለውም የፌዴራሊዝም ሥርዓት ሰላምን ከመገንባት  አንጻር ዕድሎችን፣ ተግዳሮቶችንና የችግሮች አፈታት መፍትሄዎችን ያካተተ አማራጭ ነውም ብለዋል፡፡   

በብዝኃነት ምንነትና ምንጭ ላይ በሠነድ የተደገፈ ማብራሪያ ያቀረቡት ሌላኛው  የሶሲዮሎጂ ትምህርት መምህር  ካንስቴ ገለቦ የብዝኃነት ምንነትና ምንጭን ሲያብራሩ ብዝኃነት በተፈጥሮ የሚገኝ ሲሆን የተለያየ ማንነትና የተለያየ ቋንቋ እንዲኖረን ተደርጎ መፈጠራችን ስለብዝኃነት ተፈጥሯዊነት መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ስናከብር አንድነታችንን ተግባራዊ እያደረግን ነው ያለው የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ሐይማኖት ማህተቤ በሰጠው አስተያየት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ መጠሪያችን እንደመሆኑ ተማሪዎች በተለያዩ ክበባት በማሳተፍና ጠንክሮ በመሥራት አንድነታችንን ለመጠበቅ ክብረ በዓሉ መልካም ዕድል የሚፈጥር ነው ብሏል፡፡

በዕለቱ የውይይት መነሻ ሠነዶች ቀርበው የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት የተደረገ ሲሆን  ከአዳራሽ ኩነት መጠናቀቅ በኋላ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ተካሂዷል፡፡ የኪነጥበብ ክበብ አበላት ዕለቱን የተመለከተ ሙዚቃዊ ድራማና ግጥም እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መዝሙር አቅርበዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ የካውንስል አባላት፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የተማሪዎች ኅብረት ተወካዮችና የሰላም ፎረም አባላት እንዲሁም የኪነጥበብ ክበብ አባል ተማሪዎች በመርሃ ግብሩ ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት