የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ምድር ጥናት ት/ክፍል በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች አጠቃላይ የመሬት መንሸራተት አደጋ ካርታ ሥራ እና አደጋ የመቀነስ ስትራቴጂ ጥናት ሜጋ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ኅዳር 22/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በዩኒቨርሲቲያችን ከሚሠሩ የምርምር ዓይነቶች መካከል ከፍ ያለ የግራንድ ምርምር ፕሮጀክት ነው፡፡ የምርምር ፕሮጀክቱ በዋናነት የሚያተኩረው በጋሞ ደጋማ አከባቢዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ የሚከሰትባቸው ቦታዎችን በመለየት በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመቀነስ እንዲሁም የአሁኑን ችግር ብቻ ሳይሆን የወደ ፊቱንም በማሰብ ተጋላጭ ቦታዎችን በጥናት መለየት የግድ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ቦታዎች ላይ መሰል ችግር የሚከሰት በመሆኑ የሕዝብ አሰፋፈር፣ የውሃ ጥበቃና የአፈር ናዳ መከላከያ ሥራዎችን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶና አጠናክሮ እንዲሠራ ማሳያ ፕሮጀክት መሆኑንም ም/ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ 1.75 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦለት በጋሞ ደጋማ አከባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ መንስዔዎች፣ የስጋት ቦታዎች፣ የመከላከያ ስትራቴጂዎች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥና መሠረታዊ ጉዳዮች በማጥናት መለየት የምርምሩ ዋና ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት የአደጋ ቅድመ መስጠንቀቂያና አስቸኳይ ምላሽ ቡድን መሪና የጽ/ቤቱ ተወካይ አቶ ቃይሴ ቀዲዳ እንደገለጹት በጋሞ ዞን ደጋማ አካባቢዎች በየዓመቱ በዝናብ ወቅት በመሬት መንሸራተት ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ የሆነ አደጋ እየደረሰ የሚገኝ በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ ይገኛል፡፡ በአካባቢዎቹ በሚፈጠረው የመሬት መንሸራተት አደጋ በ2013 ዓ/ም የ37 ሰው ሕይወት የጠፋ ሲሆን በ2016 ዓ/ም መጀመሪያ አካባቢም 428 አባወራዎች ወይም 2,246 ሰዎች ተፈናቅለው ይገኛሉ ብለዋል፡፡ አቶ ቃይሴ ፕሮጀክቱ በአካባቢዎቹ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋን ከመከላከል አንጻር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ዞኑ ትኩረት በመስጠት ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን የአካባቢውን ማኅበረሰብና ሌሎች አጋዥ ድርጅቶችን በማስተባበር ይሠራል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የጥናቱ ተመራማሪ ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን እንደገለጹት በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች ያለውን ሰፊ የመሬት መንሸራተት አደጋ በመለየት በማኅበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን የሰውና የእንስሳት ሕይወት ማጣት፣ የመንገዶች መበላሸትና መሰንጠቅ፣ የገበሬው እርሻ ቦታ መበላሸትና ምርት ማጣት የመሳሰሉ ችግሮች ላይ ለማጥናት ፕሮጀክቱ በዩኒቨርሲቲው ደረጃ የሚከናወን ነው፡፡ በአካባቢው ያሉ ችግሮችን በመለየት በተለያየ ደረጃ አደጋው የሚከሰትበትን ቦታ ካርታ በማዘጋጀት እንደማሳያ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንና በፕሮጀክቱ የመፍትሄ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ምድር ጥናት ት/ክፍል ኃላፊና የጥናቱ ተመራማሪ ዶ/ር ልዑልዓለም ሻኖ በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች ዝናብ በመጣ ቁጥር ለሕዝቡ ስጋት የሆነውን ችግር ለመቅረፍ ፕሮጀክቱ መቀረጹን ገልጸዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው የተፈጥሮ አደጋን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም አደጋውን ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ትኩረት በመስጠት የሚሠራ ሲሆን ለዚህም በዩኒቨርሲቲው ከተመደበው 1.75 ሚሊየን ብር መነሻ በጀት በተጨማሪ ከማኅበረሰቡና አደጋፊ ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚሠራ ይሆናል፡፡

በፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የት/ክፍሉ መምህራን፣ ተመራማሪዎች፣ ከጋሞ ዞን ግብርና መምሪያና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት የአደጋ ቅድመ መስጠንቀቂያና አስቸኳይ ምላሽ ጽ/ቤት የመጡ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት