የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት በዓለም አቀፍ ደረጃ 32ኛ እና በሀገራችን 18ኛውን የነጭ ሪባን ቀን ‹‹መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ጾታዊ ጥቃትን ዝም አንበል!!›› በሚል መሪ ቃል ከኅዳር 16-ታኅሣሥ 01/2016 ዓ/ም በአምስቱ ካምፓሶች የሚገኙ ተማሪዎችንና የአስተዳደር ሠራተኞችን በማሳተፍ አክብሯል፡፡ በአከባበሩ በሴቶች ላይ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መንስኤና የሚያስከትለው ችግር ላይ አጠር ያለ ሥልጠና፣ ውይይት እንዲሁም የተለያዩ ሥነ ጽሑፎች በተማሪዎች ቀርበዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደገለጹት የነጭ ሪባን ቀን ወንዶች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል አጋርነታቸውን የሚገልጹበትና በሴቶች ላይ ጥቃት ላለመፈጸም ሲፈጸምም በዝምታ ላለማለፍ ቃል የሚገቡበት ነው፡፡ በሴቶች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በአብዛኛው ጥቃት አድራሾቹ ወንዶች በመሆናቸው ይህንን ለማስቆም ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባ ዳይሬክተሯ አሳስበዋል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ በዓሉ ሲከበር ወንዶች ነጭ ሪባን ደረታቸው ላይ በማድረግ የሴቶችን ጥቃት በመከላከል ሂደት ውስጥ አጋርነታቸውን እንደሚያሳዩ ብሎም በሴቶች ላይ ጥቃት ላለማድረስ እንዲሁም ጥቃት ሲደርስባቸው ዳር ቆሞ ላለመመልከት ቃል እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡ እንደ ቡድን መሪው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በብዙ መልክ ሊገለጽ የሚችል ሕገ ወጥ ድርጊት ሲሆን ሴት ሕፃናትና እናቶች በጾታቸው ምክንያት ለሚፈጸምባቸው አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶች ይጋለጣሉ፡፡ አቶ ዛፉ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መነሻቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት መሆኑን በመረዳት ጥቃቶችን ለማስቆም በኃላፊነት መታገል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በተዛባ የሥርዓተ ጾታ አመለካከት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች ጥቃት ሊቆም አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱን ለማስቆም አመለካከትን ማስተካከልና ግንዛቤን ማሳደግ ይገባልም ብለዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ በበኩላቸው እንደ ታዳጊ ሀገር በተለያዩ ግለሰቦች በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጥቃት የሚደርስ በመሆኑ በሀገር አቀፍ፣ በተቋምና በግለሰብ ደረጃ ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ትኩረት ሰጥቶ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር ረ/ፕ ድንቅዓለም ጌታሁን አጠር ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ትርጉም፣ መነሻ፣ ዓይነቶች፣ በሥራ አካባቢ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዴት መከላከል ይቻላል የሚሉ ሃሳቦች እንዲሁም ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች የሚያስፈልጋቸው አገልግሎት በሥልጠናው ከተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሁሉም ማኅበረሰብ በባለቤትነት ትኩረት ሰጥቶ ሊከላከልና ሊሠራበት እንደሚገባ የበዓሉ ታዳሚዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የተዛቡ የሥርዓተ ጾታ አመለካከቶችን ለመቅረፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች አንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት