የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የጋሞ ዞንንና የካምባ ዙሪያ ወረዳ አመራሮች ዩኒቨርሲቲው ከክርስቲያን ኤይድ ጋር በመተባበር በ9.35 ሚሊየን ብር በካምባ ዙሪያ ወረዳ ዲንጋሞ ቀበሌ ማይጸሌ ወንዝ ላይ እያስገነባ የሚገኘውን የዲንጋሞ አነስተኛ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸምን ኅዳር 29/2016 ዓ/ም ምልከታ አድርገዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የፕሮጀክቱ ማኔጀርና የታዳሽ ኃይል ተመራማሪ አቶ በየነ ፈዬ ስለፕሮጀክቱ አፈጻጸምና አሁናዊ ሁኔታ ባቀረቡት ሪፖርት ፕሮጀክቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታስቦ ሰኔ 12/2014 ዓ/ም በይፋ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡ በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ተግዳሮቶች ምክንያት ሥራውን በተባለው ጊዜ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ የጠቆሙት አቶ በየነ አሁን ላይ አብዛኛው ሥራዎች ተጠናቀው አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 88 ከመቶ መድረሱንና በሦስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ በየነ የግንባታ ግብዓቶችን ለማጓጓዝ የሚያግዙ ተሽከርካሪዎች እጥረት፣ የግንባታ ግብዓቶችና የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናር፣ ድንጋይና አሸዋ የመሳሰሉ ግብዓቶች በአካባቢው በቅርበት አለመኖር፣ የአካባቢው የመሬት አቀማመጥና መንገዱ የግንባታ ግብዓቶችን ለመጓጓዝ ምቹ አለመሆን እንዲሁም በአካባቢው የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ በሥራው ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ፕሮጀክቱ በተባለው ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ያደረጉ ችግሮች ናቸው፡፡

ለፕሮጀክቱ ከተመደበው 9.35 ሚሊየን ብር 7.5 ሚሊየን ያህሉ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ቀሪ የሲቪልና ኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ በየነ ጠቁመዋል፡፡ የመብራት ፖሎች፣ ፔንስቶክ፣ ተርባይንና ሌሎች ኤሌክትሮሜካኒካል ግብዓቶችን ማጓጓዝና ተከላ ማከናወን፣ የመብራት ኬብልና ትራንስፎርመር ግዥ መፈጸምና ዝርጋታ ማከናወን፣ ቀሪ የካናል፣ ሪዘርቫየርና ፓወርሀውስ ሥራዎችን ማከናወን ከፕሮጀክቱ ቀሪ ሥራዎች መካከል መሆናቸውን የገለጹት አቶ በየነ እነዚህንና ሌሎች ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን 3.6 ሚሊየን ብር ያህል እንደሚያስፈለግ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የዲንጋሞ አነስተኛ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የዩኒቨርሲቲው ተልእኮዎች የሆኑትን ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማኅበረሰብ ጉድኝትን አካቶ የያዘ መሆኑንና ከዲዛይን እስከ ግንባታ ድረስ ያለው ሂደት ሙሉ በሙሉ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የተመራ መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ዲንጋሞን የመብራት ኃይል ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ዳምጠው ዩኒቨርሲቲው ለቀሪ ሥራዎች የሚሆኑ አስፈላጊ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ እዚህ ደረጃ መድረስ የበኩላቸውን ለተወጡ የፕሮጀክቱ መሓንዲሶች፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የዲንጋሞ አነስተኛ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው በልዩ ትኩረት የሚደግፈው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከምልከታው መልስ እንደ ዩኒቨርሲቲ ውይይት በማድረግ ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የሚያግዙ ድጋፎች እንደሚደረጉ የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ለሥራው መጠናቀቅና እውን መሆን አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪና የአስተዳዳሪው ተወካይ አቶ በርገና በቀለ እንደተናገሩት በዞኑ በርካታ አካባቢዎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የራቁ በመሆናቸው የመብራት ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ ሲሆን የዲንጋሞ ፕሮጀክት እውን ከሆነ መሰል ሥራዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት የሚያስችል ጥሩ ተሞክሮና ትምህርት የሚገኝበት ነው፡፡ በምልከታቸው ከጥቂት ሥራዎች ባሻገር አብዛኛው የፕሮጀክቱ ሥራ መጠናቀቁን ማረጋገጣቸውን የገለጹት አማካሪው ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው በማሳሰብ በቀሪ ሥራዎች ላይ የዞኑ መንግሥት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ፕሮጀክቱ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ የሚደነቅ ነው ያሉት የካምባ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተካ ውዴ የወረዳው አስተዳደር ፕሮጀክቱን በትኩረት እየደገፈ እንዲሁም ማኅበረሰቡን በማስተባበር ረገድ የበኩሉን እየተወጣ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በተባለው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቅቅ እንዲሁም በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚገኙ የእርሻ ማሳዎችን ወደ አፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ውስጥ ለማስገባት የበኩሉን እንደሚወጣና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የምርምር ማዕከላት ዳይሬክተሮችና የዘርፉ ምሁራን፣ የጋሞ ዞንና የካምባ ዙሪያ ወረዳ አመራሮች፣ የዲንጋሞ ቀበሌ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት