አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ 32 እና በኢትዮጵያ 31ውን የአካል ጉዳተኞች ቀን ‹‹ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር›› በሚል መሪ ቃል ኅዳር 23/2016 ዓ/ም አክብሯል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ካፒታ ባልቻ እንደገለጹት ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የመኝታ፣ የመረማመጃ ቦታዎችና ሌሎች አገልግሎቶችን ምቹ ማድረግ፣ ነፃ የፎቶ ኮፒ አገልግሎት፣ ልብስ ማጠብ ለማይችሉ ተማሪዎች ልብስ እጥበት አገልግሎት እንዲያገኙ ማመቻቸት እንዲሁም መገለልና መድልኦ እንዳይደርስባቸው ከላይኛው እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ ኃላፊዎች ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው፡፡ እንደ አቶ ካፒታ በየዓመቱ በአካል ጉዳተኞች ቀን ዕለቱን በማስመልከት የተፈጥሮ መስህቦች ጉብኝትና በአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችና ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማካሄድ ዕለቱ ይከበራል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የልዩ ፍላጎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ ድንበሩ የኋላእሸት በዓሉ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ለማስገንዘብ ብሎም ተማሪዎቹ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንደመሆናቸው የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት እንዲጎበኙ የሚመቻችበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ደኅንነት በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ማስተዋወቅና ግንዛቤን ማሳደግ የበዓሉ ዓላማ መሆኑንም አቶ ድንበሩ ገልጸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች፣ ከዩኒቨርሲቲውና ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች የመጡ ሠራተኞች፣ የሥራ ክፍል አስተባባሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የኪነ ጥበብ ቡድን የተለያዩ አዝናኝ ሥነ ጽሑፎችና ድራማ አቅርቧል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት