በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዕድሜያቸው ከ10-19 ዓመት በሆኑ አፍላ ወጣቶች ዲጂታል ሄልዝ አገልግሎትን በመጠቀም የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት አወሳሰድን ማሻሻል ላይ በማተኮር የተከናወነ የምርምር ሥራን አስመልክቶ ታኅሣሥ 6/2016 ዓ/ም የምርምር ማስተዋወቂያ ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ የምርምር ሥራው በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማኅብረሰብ ጤና ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም ስዊድን ሀገር በሚገኘው ለንድ ዩኒቨርሲቲ/Lund University/ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ዓባይነህ ቱንጄ የተሠራ ነው፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለጹት ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን የዲጂታል ሄልዝ አገልግሎት የጤናና ሕክምና ሥርዓቱን ከማሻሻል ባሻገር ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብን ይቆጥባል። ይህ ዘዴ በተወሰነ ደረጃ በሀገራችን በከተሞች አካባቢ ተግባራዊ ይደረጋል ያሉት ዶ/ር ታምሩ አሁን ላይ ይፋ የተደረገው የምርምር ውጤት ዘዴውን ከማስፋፋት አንጻር የጎላ ሚና የሚጫወት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ዓባይነህ ቱንጄ የምርምር ውጤታቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ዕድሚያቸው ከ10-19 ያሉ ታዳጊ ወጣቶች መድኃኒት መውሰድን በመርሳት፣ ሊደርስባቸው የሚችል መገለልን በመፍራት እና በሌሎች ምክንያቶች የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒትና ሕክምናን በአግባቡ አይወስዱም፡፡ መድኃኒቱን በአግባቡ አለመውሰድ  መድኃኒቱ ከሰውነት ጋር እንዲላመድ እንደሚያደርግ እንዲሁም በሰውነት ውስጥ የቫይረሱን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር የቫይረሱን በቀላሉ ወደ ሌሎች ሰዎች የመተላለፍ ዕድል ከፍ እንደሚያደርግ ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ ይህም ሁኔታ ሕሙማኑን ለከፍተኛ የጤና መታወክና በሂደት ለሞት ጭምር ሊዳርግ ይችላልም ብለዋል፡፡

እንደ ተመራማሪው ቴክኖሎጂን ወይም የዲጂታል ሄልዝ አገልግሎትን በመጠቀም የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት አወሳሰድ ሁኔታን ማሻሻልን ዓላማ በማድረግ በጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ጥናታቸውን አከናውነዋል፡፡ የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት አወሳሰድን ለማሻሻል በዓለም ጤና ድርጅት ከሚመከሩ ስልቶች መካከል አንዱ የማስታወሻ አጭር የጽሑፍ መልእክት መጠቀም ሲሆን በጥናታቸው የሞባይል ስልክን በመጠቀም ታካሚዎች መድኃኒታቸውን በሰዓቱ እንዲወስዱ ለማታወስና በቀጠሮ መሠረት ሕክምናቸውን በሚከታተሉበት ተቋም ተገኝተው ሕክምናቸውን እንዲቀጥሉ ለማስቻል በጥናቱ ለሚሳተፉ ታካሚዎች ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባባር አጭር የጽሑፍ መልእክት መላኪያ ሥርዓት በመንደፍ ለ6 ወራት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በዚህ ዘዴ የታካሚዎች መድኃኒት አወሳሰድ 34 በመቶ ያደገ ሲሆን በደም ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ ጫና ወይም መጠን 30 በመቶ የቀነሰ መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡን ተመራማሪው አክለዋል፡፡

ጥናታቸው ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሀገሪቱን የጤናና ሕክምና ሥርዓት ከማሻሻል አንጻር የጎላ ሚና ሊኖረው እንደሚችል የተመለከተበት እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪው መሰል ዘዴዎችን በመደበኛው የጤና ሥርዓት ውስጥ አካቶ የመጠቀም ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ በጥናታቸው የተጠቀሙት ለታካሚዎች የማስታወሻ አጭር መልእክት በስልክ የመላኪያ ዘዴ ለአሠራር እንዲሁም ከወጪ አንጻር እጅግ ቀላልና ከመንግሥት አቅም በላይ አለመሆኑን የገለጹት ተመራማሪውየሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ዘዴው በጤና ተቋማት ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ብቻ ሳይሆን የሌሎች በሽታዎችን ሕክምና አሰጣጥ ማሻሻል እንደሚችሉ መክረዋል፡፡

ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል ከጋሞ ጤና መምሪያ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ወ/ሮ ንግሥት ዘርይሁን የመድኃኒት ሰዓት መርሳት በፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት አወሳሰድ ላይ የሚስተዋል ዋነኛው ችግር በመሆኑ በጥናቱ በየዕለቱ የማስታወሻ መልእክት በመላክ የተሠራው ሥራና የተገኘው ውጤት የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እንደ ባለሙያዋ በጥናቱ የተሞከረው የዲጂታል ሄልዝ አገልግሎት ታካሚዎች ከመድኃኒት ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማሻሻል ረገድ የጎላ ሚና ያለው በመሆኑ አሠራሩን የማስቀጠል እንዲሁም በሁሉም ጤና ተቋማት ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት