የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ፈረንሳይ ሀገር ከሚገኝ ‹‹Fund for Innovative Development (FID)›› ድርጅት ጋር በመተባበር በሚያከናውነው ‹‹Adoption of Rhizobium Inoculant Technology (ARIT)›› የተሰኘ የትብብር ፕሮጀክት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ‹‹Bio-Fertilizer›› ማምረት ላይ የለውጥ ማሳያ (Progress) ሪፖርትና የመስክ ምልከታ ታኅሣሥ 4/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በትብብር ፕሮጀክቱ ባቄላ፣ አኩሪ አተር፣ ቦሎቄ፣ ሽምብራ፣ አተርና ሌሎች ጥራጥሬዎች/Leguminous Plants/ ለማምረት የሚያገለግል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለሙከራ የሚመረትበትና ማዳበሪያው በማሳ ላይ በተክሎቹ ላይ የሚሞከርበት የምርምር ማሳያዎች የመስክ ምልከታ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ምርምሩን በማሳደግ ለአርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በተለያየ መልኩ ለማቅረብ እንዲሁም መሰል ምርምሮችንና ፕሮጀክቶችን ለማሳደግ እንደሚሠራ ዶ/ር ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡

በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የባዮሎጂ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር አሽናፊ ኃይሉ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመታት ቆይታ የደረሰበት የአፈጻጸም ደረጃ፣ የተገኙ ውጤቶች፣ የገጠሙ ችግሮችና ቀጣይ ሥራዎች ላይ ሃሳብ ለመለዋወጥ ብሎም በኮሌጁ ግቢ ውስጥ የተደራጁ የሙከራ ቦታዎችና መስክ ላይ ያሉ ምርቶችን በመመልከት ለቀጣይ ሥራ ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶችን ለማግኘት መርሃ ግብሩ ተዘጋጅቷል፡፡

እንደ ዶ/ር አሸናፊ በጥቂት በጀት ብዙ ተማሪዎችን በተግባር ማስተማር መቻሉና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማምረት ወደ ማኅበረሰቡ ለማድረስ ከሚቻልበት ደረጃ መደረሱ የፕሮጀክቱ መልካም አፈጻጸሞች መሆናቸውን የለውጥ ማሳያ ሪፖርቱና የመስክ ምልከታው ያሳያሉ፡፡ በአፈጻጸሙ እንደ ድክመት የተጠቀሱ ጉዳዮችን ለመቅረፍና በስፋት በማምረት ለማኅበረሰቡ ለማዳረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚሠሩ መሆኑንም ዶ/ር አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ፈረንሳይ ሀገር ካለ ድርጅት ጋር በጋራ እንደሚሠራና ሙሉ ወጪው በድርጅቱ እንደሚሸፈን ጠቅሰው እንደ ኮሌጅ መሰል የትብብር ሥራዎችን እናበረታታለን ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቶችን በየጊዜው የመገምገም ሥራ በዕቅድ ተይዞ የሚሠራ ነው ያሉት ዲኑ በለውጥ ማሳያ ሪፖርቱና በመስክ ምልከታው ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎች በፕሮጀክቱ እንደተሠሩ ማየት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና ተመራማሪ ቱማ አየለ መሰል ምርምሮችን የማከናወንና የምርምር ውጤቱን በሚገባ በመያዝ አባዝቶ ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ የማድረስ ሥራ ተጠናክሮ ቢሠራ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ብሎም ማዳበሪያ በውድ ዋጋ መግዛትን ለማስቀረት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

በኮሌጁ የባዮ ቴክኖሎጂ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በምርምር ሥራው ጥሩ ዕውቀትና ጠቃሚ ልምዶችን እንዳገኙ ገልጸው ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በዘርፉ ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ሥራዎች ለመሥራት መነሳሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የጋሞ ዞን ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል አመራሮች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት