18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት”በሚል ሀገራዊ መሪ ቃል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤት የአስተዳደር ኃላፊዎችን ጨምሮ ርዕሰ መምህራን፣ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት ታኅሣሥ 05/2016 ዓ.ም በድምቀት ተከብሯል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በበዓሉ ላይ የትምህርት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና በዓሉን ማክበር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ አንዱ ሌላውን እንዲረዳና እውቅና እንዲሰጥ እና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለኢትዮጵያ ልዩ ውበትና ጌጥ መሆናቸውን ትውልዱ እንዲረዳ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሥላስ የት/ቤቱ ተማሪዎች የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና ታዳጊዎች በመሆናቸው በዓሉን በዚህ መልክ ማክበር ተማሪዎቹ አከባበሩን በይበልጥ እየተረዱ እና በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እያገኙ እንዲያድጉ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል፡፡

በዕለቱ በትምህርት ቤቱ የማኅበራዊ ሳይንስ መምህር አክሊሉ አይሳ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በ1987 ዓ/ም ከፀደቀበት ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነትና አንድነት ምን እንደሚመስል እንዲሁም የበዓሉ መከበር ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚሰጠውን ፋይዳ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጾች አንጻር አጣቅሰው በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

በዕለቱ የድራማ፣ የባህል ውዝዋዜ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሙዚቃዎችና በዓሉን የሚያንጸባርቁ ሥነ ጽሑፎች በትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የቀረቡ ሲሆን መርሃ ግብሩ በት/ቤቱ የጂኦግራፊ መምህር ፈቃደ ወ/ሰንበት ተመርቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት