የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከወልቂጤ፣ ወራቤ፣ ዋቸሞ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ጂንካ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ለመጡ የግዥና ንብረት እና የፋይናንስና በጀት አስተዳደር ኃላፊዎች፣ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ክፍል ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የተማሪዎች አገልግሎት ኃላፊዎች፣ የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከተቸው አካላት ሙስናን መከላከልና መቆጣጠርን አስመልክቶ ከታኅሣሥ 05 - 06/2016 ዓ/ም የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥልጠና ጥራትና ተገቢነት ዴስክ ኃላፊ አቶ የኋላእሸት ደሳለኝ እንደገለጹት ኮሚሽኑ በ2015 ዓ/ም በሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች 11 የሥራ ዘርፎችን ለይቶ በ22 ዘርፎች ባካሄደው ጥናት በሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በግዥ ላይ ትልቅ ችግር እንዳለ ተለይቷል፡፡ ለዚህም ከዋና ምክንያቶች መካከል የሥነ ምግባር ግድፈት አንዱ ሆኖ በመገኘቱ ክፍተቱን በሥልጠና ለመሙላት በ2016 ዓ/ም በሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ለከፍተኛ አመራሮች የሥነ ምግባር ሥልጠና መስጠታቸውን አቶ የኋላእሸት ተናግረዋል፡፡ በትምህርት ዘርፉ በተገኘው ግኝት መሠረትና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተደረሰ መግባባት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችን ማሠልጠኑ ጠቃሚ በመሆኑ በክላስተር በማከፋፈል የመጀመሪያው ዙር ሥልጠና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተዘጋጅቷልም ብለዋል፡፡

በኮሚሽኑ የግንዛቤ ማስጨበጫና ማጎልበቻ ፕሮግራም ዴስክ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ዓለሙ ‹‹ሥነ-ምግባራዊ አመራር›› በሚል ርእስ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን ሥልጠናው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በመንግሥት ሀብትና ንብረት ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፉ ሥነ ምግባርን፣ መመሪያንና መርህን እንዲከተሉ ግንዛቤ የሚፈጥርና የመንግሥት ሀብትና ንብረት በታለመለት ዓላማና በተገቢው ቦታ እንዲውል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹በመንግሥት ግዥ ሙስናን መከላከል›› በሚል ርእስ ሥልጠና የሰጡት በኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥልጠና ባለሙያ አቶ ሀሰን መሐመድ በከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራር በተለይ በግዥ ዘርፉ ላይ የጎላ መሆኑን በ2013 እና በ2014 ዓ/ም ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት መለየቱን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው በመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በግዥ ዘርፉ ላይ የሚፈጸመውን ሙስናና ብልሹ አሠራር ለማስቀረት የሚያስችል የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ነውም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ሙስና፣ ብልሹ አሠራርና የሥነ ምግባር ችግር ለአንድ ሀገር እድገት ፀር መሆናቸውን ጠቅሰው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማረ የሰው ኃይል የሚገኝባቸው ከመሆኑ አንጻር በሥነ ምግባር፣ በሀብት አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ጥሩ ምሳሌ ሆነው መገኘት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ይህንን ለማሳካት ከሚመለከታቸው የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተሠሩ መቆየታቸውን ፕሬዝደንቱ ጠቁመው በዚህም በተቋማት ውስጥ ትርጉም ባለው ደረጃ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፀረ ሙስናና የሥነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን የሥልጠናው ዓላማ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በግዥ ላይ የሚፈጸመውን ሙስና የመከላከል አቅም በማሳደግ ከሙስናና ብልሹ አሠራር የጸዳ የግዥ ሥርዓት እንዲከተሉ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደለ ያያ ሥልጠናውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየየት በግዥ ሂደት ላይ የሚፈጸመውን ከፍተኛ ሙስናና ብልሹ አሠራር በጋራና በቅንጅት ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት