አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በአግሮፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንደስትሪ አንቀሳቃሾች በምግብ ደኅንነት አስተዳደር ሥርዓት (FSMS:ISO 22000፡2018) ዙሪያ ታኅሣሥ 08/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ ሥልጠናው በከተማው ያሉ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንደስትሪዎች የምግብ ደኅንነት አስተዳደር የጥራት ደረጃ አጠባበቅ ላይ ዓለም አቀፍ የደረጃ ድርጅት/International Standard Organization/ISO/ በሚያወጣው የጥራት ልክ በመሥራት ውጤታማ እንዲሆኑ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢንደስትሪ ዘርፉ በዕውቀት፣ በቁርጠኝነት፣ በማስተዳደር ጥበብ፣ በጀትን በማሳደግና በመደጋገፍ ቢሠራበት ለብዙዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና የሀገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚቻል የተናገሩት ዲኑ የምግብ ደኅንነት የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነትና የሕይወት ጉዳይ ጭምር በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ሥልጠናው በዳቦ፣ ሞሪንጋ ማቀናበር፣ የሙዝ ዱቄት ምርት፣ ወተት፣ ጁስ እንዲሁም በኬክ ሥራ ለተሰማሩ ከ17 ማኅበራት ለተወጣጡ የማኅበር አባላት መሰጠቱን የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ወ/ማርያም ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናውን የሰጡት የኮሌጁ መምህራን የዓለም አቀፍ የደረጃ ድርጅት(ISO) ሥልጠና የወሰዱ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው እንደ ማኅበረሰብ ጉድኝት መሰል ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በስፋት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በአግሮፕሮሰሲንግ የፋርማሲቲካል ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ታምራት ዘገየ እንደገለጹት በማኅበራት የተደራጁና የግል አምራቾች ከጥቃቅን ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ እንዲሁም ከከፍተኛ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገሩ በድጋፍ ማዕቀፎች በኩል የመሥሪያ ቦታ፣ የማምረቻ ዕቃዎች፣ የመሸጫ ቦታና የቢዝነስ ዕቅድ ድጋፎች ይደረጋሉ፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የባዮቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱና የኬሚካል ምኅንድስና መምህርና ተመራማሪ አቶ ፍሬው ደነቀ ለመበላሸት ቅርብ የሆኑ ምግቦች ደኅንነትን ለማስጠበቅ የማምረቻ ማሽን፣ የሠራተኞችና የአካባቢ ንጽሕና መጠበቅ፣ በአመራረት ሂደት ምግብን ሊበክሉ የሚችሉ ነገሮችን መለየት እንዲሁም አጠቃቀሙንና የተመረተበትን ቀን መግለጽ የሥልጠናው ትኩረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ሸዋንግዛው ኡርጌ ሥልጠናው ሠልጣኞች ክፍተታቸውን ያዩበትና ለሚሠሩት ሥራ ተጨማሪ ዕውቀት ያገኙበት እንደሆነ ተናግረው ከሥልጠናው በኋላ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በሥራ ሂደት ያሉባቸውን ችግሮች በመቅረፍ ለለውጥ እንዲሠሩና ወደ ዓለም አቀፍ የምግብ ጥራት ደረጃ ለመድረስ ጥሩ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ ዩኒቨርሲቲው ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት የሰጠ ሲሆን የከተማው የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ለተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ፣ ለኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ወ/ማርያም እንዲሁም ለአሠልጣኞቹ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱና አቶ ፍሬው ደነቀ የምስጋና ምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት