የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን ማኅበር ጋር በመተባበር እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ‹‹MCGee Group›› በመጡ የግንባታ ዘርፍ ነባር ባለሙያዎች አማካኝነት ለቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን፣ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ለሚማሩ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎችና በዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል በግንባታ ዘርፍ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ‹‹Risk Management for Construction Projects - A practical Insight›› በሚል ርእስ ከታኅሣሥ 11-12/2016 ዓ/ም ወርክሾፕ አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለጹት እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው ወደ ምርምር ዩኒቨርሲቲነት ያደገ ሲሆን በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከሀገሪቱ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ እነዚህን ተቋማዊ ለውጦች መነሻ በማድረግ በመምህራን ልማት፣ በምርምርና ማኅብረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ውጤታማትን ለማሻሻልና ተወዳዳሪ አማካሪ ድርጅቶችን ለመመሥረት ከተለያዩ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች እና ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ዶ/ር ሙለነህ ጠቅሰዋል፡፡

እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ‹‹MCGee Group›› የመጡትና ሲኒየር የኮንስትራክሽን ባለሙያ አቶ ለም በሪሁን ሥልጠናው በግንባታ ፕሮጀክቶች ከመነሻ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ሊያጋጥሙ በሚችሉ አደጋዎች አስተዳደር ዙሪያ እንግሊዝ ሀገር ከገጠሙ ችግሮች የተወሰዱ መፍትሔዎችና ሳይንሳዊ ግኝቶች ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ለሠልጣኞች ልምድና ዕውቀት ለማሸጋገር የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል በኢንስቲትዩቱ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ቴክኖሎጂ ፋከልቲ መምህር ዶ/ር ፍስሃ ሳህሌ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው በሥልጠናው በግንባታ ሂደት ውስጥ ከዕቅድ አስከ ፍጻሜ ድረስ የሚገጥሙ ችግሮችንና መፍትሔዎችን በስፋት ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

የከርሰ ምድር ውኃ ምኅንድስና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ተስፋዬ ሀብቴ በሰጠው አስተያየት ሥልጠናው በተለይ በሲቪል ምኅንድስና ዘርፍ ለሚሠሩ ባለሙያዎች በሥራ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስና ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማስተዳደር የሚጠቅም እንደሆነ ተናግሯል፡፡

“Risk Management Introduction››፣ ‹‹Risk Perception Discussion››፣ ‹‹Importance of Risk Management on Construction Projects››፣ ‹‹Risk Management categories››፣ ‹‹Recap-Risk Management process Case studies››፣ ‹‹Quantification of risk Recap and Discussion››፣ ‹‹Quantifying Risk and Decision Making›› እና ‹‹Design Management as key Tool of Risk Management›› ሥልጠናው ከተሰጠባቸው ርእሶች መካከል ሲሆኑ በወርክሾፑ ከአምስቱ ፋከልቲዎች የተወጣጡ ሠልጠኞች ተሳትፈዋል፡፡ ለምኅንድስና ሳይንስ ዘርፍ የሚጠቅሙ 100 መጻሕፍትም ከአሠልጣኞች ለኢንስቲትዩቱ ተበርክተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት